ሱዳን እና ኢትዮጵያ በብሉ ናይል ወታደራዊ ንግግር ማካሄዳቸው ተዘገበ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

የብሉ ናይል አስተዳደር የሆኑት ሁሴን ያሲን በኢትዮጵያ  በ12 ኛው ክፍለ ጦር እና በሱዳን የ4ኛ ክፍለ ጦር የጦር አዛዦች መካከል በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ሁሴን ያሲን በስብሰባው ላይ በመገኘት ባሰሙት ንግግር ይህን በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገውን ወታደራዊ ግኑኝነት ስብሰባ እንዲሳካ ትብብርና ድጋፍ ላደረጉት እንዲሁም ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት ለሁለቱ አገራት መሪዎች ማለትም ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ለሱዳኑ ፕሬዚደንት ኡመር አልባሽር ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

የብሉ ናይል አስተዳዳሪ የሆኑት ሁሴን ያሲን በሁለቱ አገራት መካከል ባለው የድንበር ግኑኝነት ያለውን ሂደት እንዲያፋጥኑ የቤንሻንጉል ጉምዝ አስተዳደር በሆኑት አልሻዛሊ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠሩባቸው እንደሆነ ሱና (SUNA) የተባለው የዜና ወኪል መግለጹ ታውቋል። ሁሴን ያሲን በሁለቱ አገራት ድንበር መካከል ያለውን ደህንነት ለማጠናከርና ለማረጋጋት ባላቸው ፍላጎት ድጋፍና ትብብር እንድሚያደርጉም ገልጸዋል።

የዚህ ስብሰባ ውጤት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግኑኝነት የሚያጠናከርና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ግኑኝነት እንደሚፈጥር ተስፋቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

የሱዳኑ 4ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አሕመድ ሞሐመድ ቃሒር አል አወድ በኢትዮጵያ በኩል የድንበር አካባቢ መረጋጋት ለማጠናከር ትብብር እና ድጋፍ እንደሚያደርጉ በከፍተኛ ስሜት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም በኩል የ12ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር  ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ብርሃኑ በሱዳኑ የቶር አዛዥ በኩል የቀረበውን የትብብር እና በጋራ የመሥራትን ሃሳብ ሲቀበሉ በደስታ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሁለቱ አገሮች ወታደራዊ ግኑኝነትን በተመለከተ በ2009 ዓ.ም ወታደራዊ ፕሮቶኮል ስምምነት መሠረት ለ 3 ዓመታት የሚቆይ በጋር የድንበር ደህንነትን የማስጠበቅ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በመስከረም ወር የሱዳን እና የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኮሚሽን በሁሉም አይነት የ2009 ዓ.ም የወታደራዊ ፕሮቶኮልን ጨምሮ በ5 ዓመት እቅድ በማሳደግ መፈራረማቸው ይታወቃል።

በጥቅምት ወር ላይ ሁለቱ አገራት በጋራ በአዘጋጁት የስምምነት ሰነድ  በሁለቱ አገራት መኻከል ስለሚኖረው ደህንነት እና ወታደራዊ ትብብር በጋራ የሽብር ጥቃትን ለመጠበቅ መፈራረማቸው ይታወቃል።

በ2016 14ኛው የሱዳን እና የኢትዮጵያ የጋራ ቴክኒካል ኮሚቴ በሱዳን ካርቱም በተካሔደው ስብሰባ ከሁለቱ አገራት የተውጣጣ የጋራ ጦር በድንበር አካባቢ ለማስፈር እቅድ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱት የነፃነት ኃይሎች ከፍተኛ ስጋት ስለሆኑበት፤ ሰላም እና መረጋጋት ለማስጠበቅ በሚል ሰበብ  ከሱዳን ጋር የሚያደርገው ስምምነት እነዚህ የነፃነት ኃይሎች በስፍራው እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ያቀደው እንደሆነ የሚሉ ትንታኔዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።

ሱዳን እየዋለችለት ላለው ውሎታ አገዛዙ የኢትዮጵያን መሬት በስጦታ መልክ በመስጠት እንደሚደራደር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።