ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ የተባለው ስህተት ነው (የጠቅላይ ሚንስትሩ ረዳት)

አባይ ሚዲያ ዜና 

ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱና የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያ (ማእከላዊ እስር ቤት) እንደሚዘጋ ረቡዕ እለት የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ስህተት እንዳለበት ረዳታቸው ለውጭ ሚዲያዎች አሳወቁ።

ቢቢሲ (BBC) “Ethiopia to release political prisoners, says prime minister” በሚል ርእስ ረቡዕ እለት ባወጣው ዘገባ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ ተብሎ በዜና ተቋማት የተሰራጨውን ዜና የጠቅላይ ሚንስትሩ ረዳት እንዲሻሻል መጠየቃቸውን እና “Ethiopia PM ‘misquoted’ over prisoners” ትብሎ እንዲታረም ይህ የዜና አውታር አስነብቧል።

በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስር ተዳርገው እየተሰቃዩ ያሉትን ሁሉም እስረኞች ነጻ ይለቀቃሉ ተብሎ በተለያዩ ዜና አውታሮች የተላለፈው መግለጫ የትርጉም ስህተት እንዳለበት የጠቅላይ ሚንስትሩ ረዳት መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች በምህረት ነጻ ይለቀቃሉ የተባለውን ዜና መንግስት እንደካደ ቢቢሲ (BBC) በመጥቀስ ሁሉም ሳይሆን የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞችን ብቻ እንደሆነ ይህ የዜና አውታር በእንግሊዘኛ ዘገባው “Ethiopia’s government has denied that all political prisoners will be freed, saying that only some imprisoned politicians will be pardoned” በማለት አስፍሮታል።

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ነጻ እንደሚለቀቁ ከዘገቡት የዜና አውታሮች መካከል የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን (The Guardian) “Ethiopia says it will free all political prisoners”፣ መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ  ያደረገው ‘National Public Radio’ የተባለ የሬዲዮ ጣቢያ እንዲሁም ዋና ቢሮውን በቱርክ አንካራ ያደረገው ‘Anadolu Agency’  ይገኙበታል።

‘The New York Times, ABC News, Boston 25 News’ እያንዳንዳቸው በረቡዕ ዘገባቸው “Ethiopia to release all political prisoners, close camp” በሚል ርእስ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁሉም እስረኞች እንደሚፈቱ ያዘጋጁትን ሃተታ ለአንባቢያን አቅርበዋል። 

የጠቅላይ ሚንስትሩ ረዳት ማስተካከያ እንዲደረግ ከመጠየቃቸው በፊት አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ እንዳሉ የጀርመን ሚዲያዎችም “Ostafrika Äthiopien verspricht Freilassung aller politischer Gefangenen” በሚል ርእስ  ለአንባቢያን አቅርበዋል። 

ከዚህ በፊት የፖለቲካ እስረኛ በአገሪቷ ውስጥ የለም በማለት አገዛዙ ሲናገር እንደቆየ እነዚህ አለም አቀፍ ሚዲያ በዘገባቸው በማስታወስ  መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር የዳረጋቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ረቡዕ እለት ማሳወቁ እርስ በእርሱ የሚጋጭ መግለጫ እንደሆነ የዜና አውታሮቹ ለማሳየት ሞክረዋል።

አለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉንም እስረኞች እንደሚፈቱ በረቡዕ እለት የዜና ዳሰሳቸው ያሰፈሩትን ዘገባ “የተወሰኑ እስረኞች” በሚል እንዲቀየር የጠቅላይ ሚንስትሩ ረዳት ባቀረቡት ጥያቈ መሰረት ዜናውን አሻሽለው አቅርበውታል።