እስከ የሚቀጥለው ቅዳሜ የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

የፕሬዘዳንቱ ጽ/ቤት የፖለቲካ እስረኛ የሆኑ የፓርቲ አመራሮችና አባላት ሰም ዝርዝር እንዲቀርብለት መመሪያ ሰጠ፤ ይሁንና ምን ያህሎቹ እንደሚፈቱ ባይታወቅም በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተዘገበ፡፡

ለመንግስት ቅርበት እንዳለው የሚታወቀው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ መግለጫ ሰጡ። በማግስቱ ደግሞ የፕሬዘዳንቱ ጽ/ቤት የማረሚያ ቤት አስተዳደር ፍርደኛ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ስም ዝርዝር እንዲቀርቡለት አዟል። ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙትን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲያቀርብ መመሪያ የደረሰው ሲሆን፣ እስረኞቹ እስከ የሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ታውቋል፡፡

ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ከሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ውስጥ ዶ/ር መረራ ጉዲናና አቶ በቀለ ገርባ ይገኙበታል። በተጨማሪም ሌሎች በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን የሚከታተሉና ተፈርዶባቸው በወህኒ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላቶችና ጋዜጠኞች በርካታ መሆናቸው ይታወቃል፤ ይሁን እና ከነዚህ እስረኞች መካከል በትክክል ምን ያህሉ እንደሚፈቱ የታወቀ ነገር የለም፡፡