ወደ 600 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን ከኖርዌይ ለማስወጣት እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

የ’FRP’ (Fremskrittspartiet/The Progress Party) ፖለቲከኛ እና የስደተኞች ሚኒስትር፣ ሲልቪ ሊስትሃውግ፣ ከ600 በላይ የሚሆኑ ፈቃድ የተከለከሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው በሚል አቋም አዲስ አበባ ገብተዋል።

ኖርዌይና ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራቸው ስደተኛ የመቀበል ስምምነት ከአንድ አመት በፊት ያለቀ ሲሆን፥ ያ ስምምነት ለኖርዌይ የሚፈልጉትን ውጤት እንዳላመጣላቸው ይታወቃል። ይህም የሆነበት ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት(የኢትዮጵያ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት) ስለተመላሾቹ የሚቻለውን ያህል መረጃ ያስፈልገኛል በማለቱ እና የኖርዌይ መንግስት ደግሞ እነዚህን መረጃዎች አሳልፎ የመስጠት መብት ስላልነበረው ነበር።

ሊስትሃውግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከቀድሞው የተሻለ ስምምነት ላይ ለመድረስ በአሁኑ ሰአት ድርድር ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ምን ትጠቀማለች ለሚለው ጥያቄ ሚኒስትሯ ሲመልሱ፣ በአሁኑ ሰዓት የተወሰነ ነገር የለም፣ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ከትምህርት፣ ከአየር ንብረት እና ከጤና ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶች አሉን፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ትብብር አለን። ኖርዌይ በተለይ ለኢትዮጵያ ብዙ እርዳታ እያደረገች መሆኑ ሲታወቅ፣ ኢትዮጵያ ከአገራችን ጋር ባላት የሁለትዮሽ ግንኙነት በ2016እኤአ 55.5 ሚሊዮን ዶላር  አግኝታለች። በአጠቃላይ እነዚህ ሁለገብ ትብብሮች ዛሬ ለምናደርገው ድርድር አጋዥ ሊሆኑ ይችላሉ። ኖርዌይ በምታደርገው ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት ደስተኛ እንደሆነም ተረድተናል ብለዋል።