አባይ ሚዲያ ስፖርት ዜና

በሚያስደንቅ ያለመሸነፍ ጉዞ የፕሪሚየር ሊጉን ውድድር ሲገሰግስ የቆየው የፔፕ ጋርዲዮላ ማንችስተር ሲቲ በሊቨርፑል ክፉኛ ፈተና ገጥሞታል።

ማንችስተር ሲቲን ያስተናገደው ሊቨርፑል በጥሩ ጨዋታ 4 ጎሎችን ከመረብ በማሳረፍ ባጠቃላይ 4 ለ 3 በሆነ ውጤት በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ማንችስተር ሲቲ እንዲሸነፍ አድርጎታል።

“ሊቨርፑል ክለብን እንኳን ደስ አላችሁ እላለው፤ 1 ለ 1 በነበርንበት ወቅት ጨዋታው በእጃችን ነበር ነገር ግን  ውጤቱም በቅጽበት ተለውጦ 4 ለ 1 ሆነ፤ አጨራረስ ላይ ችግር ታይቶብናል ” በማለት የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።

“እውነታው በዚህ ጨዋታ ተሸንፈናል፤ ከዚህ ሽንፈታችን ማገገሚያ የሳምንት ጊዜ አለን፤ ተጋጣሚያችን የጀርገን ክሎብ ቡድን አድናቆት ይገባዋል” በማለት የማንችስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ አክለው ገልጸዋል።

“ይህ ታሪካዊ ግጥሚ ነው ለሚቀጥሉት 20 አመታት ሊወራለት ይችላል ምክንያቱም ማንችስተር ሲቲ በአሁኑ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከዚህ በሃላ የሚሸነፍ አይመስለኝም” በማለት የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ጀርገን ክሎብ በውጤቱ የተሰማቸውን ደስታ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ማንችስተር ሲቲ በ 62 ነጥብ በደረጃው አናት ላይ አሁንም ሲገኝ ሊቨርፑል  በ 47 ነጥብ በ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቼልሲ ከሌስተር ሲቲ ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ጎል 0 ለ 0 ሲለያይ በደረጃ ሰንጠረዡ በ47 ነጥብ 4ኛ ላይ ይገኛል።

ሁለት ጎሎችን ሃሪ ኬን ባስቆጠረበት ጨዋታ ቶትንሃም ኤቨርተንን ባጠቃላይ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፉ በ 44 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል።

“ሃሪ ኬን ፕሮፌሽናል እና ድንቅ ብቃት ያለው ተጨዋች ነው፣ አድናቆት ሊቸረው ይገባዋል እንደውም ሁሉንም የፕሪሚየር ሊግ የጎል ሪከርዶችን ይሰብራል ብዮ ተስፋ አደርጋለው በሃሪ ኬንም ደስተኛ ነኝ” በማለት የቶትንሃሙ አሰልጣኝ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።

የአርሰን ቬንገር አርሴናል ከቦርንማውዝ ጋር ባደረገው ጨዋታ ድል ሳይቀናው ቀርቶ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። “የሰራናቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍለውናል፣ በቂ የሆነም እድል መፍጠር ተስኖን ነበር” በማለት አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በጨዋታው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። አርሴናል በ 39 ነጥብ 6 ኛ ደረጃን ሲይዝ ቦርንማውዝ በ24 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የጆሲ ሞሪኒዮ ማንችስተር ዩናይትድ ሰኞ ከስቶክ ሲቲ ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ ከመሪው ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበት ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል።