የ528 ተከሳሾች ክሳቸው ተቋረጠ፣ ከእሮብ ጀምሮ ይፈታሉ ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የ528 እስረኞች ክስ መቋረጡን አስታወቀ። ከ528 ክሶች ውስጥ 115ቱ በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ 413 ክሶች በደቡብ ክልል  የሚገኙ መሆናቸውና እስረኞቹም ከሚቀጥለው እረቡዕ ጀምሮ እንደሚፈቱ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ ገለጹ።

የፌደራሉ አቃቤ ሀግ የሆኑት አቶ ጌታቸው አምባዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በተለይ በደቡብ ክልል ክሳቸው የተቋረጠላቸው በጌዲዮ ዞንና በኮንሶ ወረዳ ተፈጥሮ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ታስረው ለነበሩ እስረኞች ነው። በፌደራልና በደቡብ ክልል ቀርበው ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ውጭ በሌሎች ክልሎች ክሳቸው የሚቋረጥላቸው እስረኞች ዝርዝር ገና ያላቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አቃቤ ህጉ በሰጡት መግለጫ ክሳቸው ተቋርጦ የሚፈቱት እስረኞች ማንነት በቀጣይ እንደሚያስታውቁና ክሳቸው የተቋረጠላቸው እስረኞች ከሚቀጥለው እረቡዕ ጀምሮ እንደሚለቀቁ አስታውቀዋል። የተፈረደባቸውን እስረኞች በተመለከተም አራት መስፈርቶች ወጥቶ በወጣው መስፈርት እስረኞችን የመለየት ስራ መጀመሩና የመለየቱ ስራ ግን ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡