በወልዲያ በደረሰው እልቂት የአርበኞች ግንቦት 7 የሀዘን መግለጫ

በወልዲያ በደረሰው እልቂት የአርበኞች ግንቦት 7 የሀዘን መግለጫ

ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም.

ቅዳሜ  ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በጥምቀት በዓል ዋዜማ ቃና ዘገሊላ ዓመታዊ በዓል ላይ የህወሓት አገዛዝ በወልዲያ ከተማ ምዕመናን ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ እስካሁን ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ወገኖቻችን ሕይወት አልፏል፤ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በአገዛዙ ፋሽስታዊ እርምጃ ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል። የእነዚህ ወገኖቻችን ሕይወት ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲሁም ለሀገር አንድነት የተከፈለ ዋጋ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 በጥልቀት ይገነዘባል።  በዚሁ የጅምላ ጥቃት ለአካል ጉዳት ለተዳረጉ ወገኖቻችንም አስቸኳይ እርዳታ የሚያገኙበት መንገድ በማመቻቸት ሁላችን የሚቻለንን እንድናደርግ  አርበኞች ግንቦት 7 ያሳስባል።

የህወሓት አገዛዝ “ስህተት ስፈፅም ኖሬዓለሁ፤ የስትራቴጂያዊ አመራር ድክመቶች አሉብኝ፤ ከእንግዲህ እነዚህን ሁሉ አሻሽላለሁ። የፓለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ፤ ማኅበራዊ መግባባትን አሰፍናለሁ…” እያለ በአደባባይ የሚደሰኩር ቢሆንም በተጨባጭ ግን ምንም  ዓይነት የፓሊሲ ወይም የባህሪይ ለውጥ ያላደረገ መሆኑን የወልዲያው ጥቃት ምስክር ነው። ህወሓት አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ በመግደል፤ ስልታዊ በሆነ  መንገድ የዘር ግጭትን በመቀስቀስ የርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርገው ሙከራ ላይ ዕለት በእለት እየተባባሰ ከመምጣቱ በስተቀር ለውጥ እንዳልታየበት የወልዲያው እልቂት ምስክር ነው። የህወሓት አገዛዝ መወገድ ያለበት እኩይ፣ ፋሺስታዊና በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተጠላ ሥርዓት መሆኑ የማያሻማ ሆኗል። የህወሓት መወገድና በምትኩ የሽግግር መንግሥት መቋቋም የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድና ወንጀለኖችን ለፍርድ ማቅረብ የቅርብ ጊዜ ግባችን ሆኗል።

ይህንን ግብ ለማሳካት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከህወሓት አገዛዝ የሚደርስበትን ጥቃት በጋራ እየተቋቋመ የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር በኅብረት እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን። በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደው የፀረ-ህወሓት ትግልን ማቀናጀት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው። በዚህ ረገድ አርበኞች ግንቦት 7 በመላ ኢትዮጵያ የሚደረገውን ትግል ለማስተባበር እየተጋ ነው፤ አብረን እንቁም።  ህወሓት እያጣጣረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ብዙ ጉዳቶችን ሊያስከትል የሚችል ከመሆኑም በላይ የእርስበርስ ግጭቶችን ለማስነሳት የማይፈለቅለው ድንጋይ አይኖርምና  እንጠንቀቅ።

ከላይ ከተብራራው የህወሓት ያልተለወጠና የማይለወጥ ፋሽስታዊ ባህሪ ሌላ የወልዲያው ጭፍጨፋ ያሳየን ተጨማሪ ሀቆች አሉ። በብአዴን ውስጥ የሕዝብ ወገኖች መኖራቸው እሙን ነው፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ወገኖች በትንሹም ቢሆን ድርጅታቸውን ከህወሓት ቀጥተኛ ተጽዕኖ ማላቀቅ እንዳልቻሉ የወልዲያው ጭፍጨፋ ምስክር ነው። ይህ ለብአዴን ማስጠንቀቂያ ነው። እንደዚሁ፤ በአማራ ክልል ፓሊስ ውስጥ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል የሚቆረቁራቸው መኖራቸው እሙን ቢሆንም ሕዝባቸውን እንዲገድሉ ከበላይ የሚደርሳቸውን ትዕዛዝ “እንቢ” የማለት አቅም አለማዳበራቸው የታየበት ነው። እነዚህ አስቸኳይ እርምት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓትን አገዛዝ ከዚህ በላይ የሚሸከምበት ትከሻ የለውም። የህወሓት አገዛዝ ጊዜው ያለበት፤ መቃብሩ የተማሰ ሥርዓት ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለውጥ ፈላጊው ኃይል ተሰባስቦ ህወሓትን እርቃኑን ማስቀረት ይኖርበታል። ስለሆነም እያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ከሚያምነው ወዳጁ ጋር  በመሆን ይደራጅ፤ በአርበኞች ግንቦት 7 መዋቅር ይታቀፍ።

የብአዴን አባላት ሚናችሁን ለዩ፤ ከሕዝብ ጎን ሁናችሁ የለውጥ አካል ካልሆናችሁ ከህወሓት ጋር መጥፋታችሁ የማይቀር ነው፤ በታሪካችሁ እናንተ ብቻ  ሳትሆኑ የልጅ ልጆቻችሁ የሚያፍሩበት ይሆናል። የአማራ ክልል የፓሊስ አባላትም በህወሓት ሹማምንትና ጄኔራሎች ትዕዛዝ ወገኖቻችሁን መግደላችሁን አቁሙ፤ ይቆጫችኋል፤ ይፀፅታችኋል፤ ዋጋ ያስከፍላችኋል።

ከዚህ በፊት በጎንደር ከተማ፣ በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) እሬቻ በዓል፣ በሶማሌ ክልክ ጅግጅጋ በወገኖቻችን ላይ በህወሓት  የተቀነባበሩ እልቂቶች በደረሱበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥም እውጭ አገራትም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞዓቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልፀዋል። ትላንት በወልዲያ ለደረሰው እልቂት ኢትዮጵያዊን ቁጣቸው በተመሳሳይ መንገድ እንዲገልፁ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።

ከወልዲያ ሰማዕታት ስርየት የሚኖረን የህወሓትን አገዛዝ አስወግደን በሕዝብ ተቀባይነት ያለው አስተዳደር ስናቆም ብቻ  ነው።

 

ዘላለማዊ ክብር ለሰማዕታት!

አንድነት ኃይል  ነው