በጸጥታ ስጋት ምክንያት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተቋረጠ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

የጥምቀት በአልን እና ነገ ይጀመራል የሚባለውን 30ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ተከትሎ የጸጥታ ችግሮች ይኖራሉ በሚል ስጋት በአዲስ አበባና አካባቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ከኮማንድ ፖስቱ ትእዛዝ ተሰጠ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለአንድ ሳምንት እንዲቋረጥም ተደረገ፡፡

የፌደራል የጸጥታ ኮማንድ ፖስት ባወጣው መግለጫ የጥምቀት በአልን እና የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን ተከትሎ የጸጥታ ችግሮች ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የደረሱኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ በዚህም መሰረት የስራ ስምሪቶች በማድረግ ላይ እንገኛለን ብሏል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ ጨምሮም በማንኛውም ሁኔታ ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ  እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፤ በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችንም ለአንድ ሳምንት እንዲቋረጡ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የህወሀት/ኢህአዴግ አገዛዝ በተለይም ህዝባዊ በአላትን እና እስፖርታዊ ውድድሮችን እየተጠቀሙ የሚነሱ ህዝባዊ እንቢተኝነቶች የፈጠሩበት ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ ተቃውሞዎቹን መቋቋም እንደተሳነው ከሚያሳዩት እርማጃዎቹ አንዱ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በርካታ ናቸው፡፡