የተባበሩት መንግስታት በወልዲያ የተፈፀመው ግድያ እንዳሳሰበው አስታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤነዘር አህመድ

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቃለ አቀባይ በወልዲያ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በዓልን ለማክበር በወጡ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈት በርካታ ሰዎችን መግደላቸው እንዳሳሰባቸው ተናገሩ።

በጄኔቫ ንግግራቸውን ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ቃለ አቀባዩዋ በወልዲያ ከተማ የፀጥታ ሃይሎች በዝማሬ ላይ በነበው ህዝብ ላይ ተኩስ መክፈታቸውን በመጥቀስ በእርምጃው የተበሳጩት ነዋሪዎች መንገዶችን በመዝጋት ቁጣቸውን ሲገልጹ እንደነበረ ሪፖርት መደረጉን ራቪና ሻምዳሳኒ ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ቅርጫፍ ቢሮ ከመንግስት ሚዲያዎች፣ ከታማኝ የሲቪል ማህበረሰብ ምንጮች እንዲሁም ከመንግስታዊ መግለጫዎች ባሰባሰበው መረጃዎች የፀጥታ ሃይሎች በወልዲያ ህዝብ ላይ በመተኮስ ግድያ መፈፀማቸውን መረዳት እንደተቻለ ቃለ አቀባዩዋ ጠቁመዋል።

መንግስት በአገሪቱ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ውሳኔ ካስተላለፈ ሁለት ሳምንታት ሳያልፈው በወልዲያ በዓልን ለማክበር በወጡ ሰዎች ላይ ጥይት በመተኮስ ግድያ መፈፀሙ እጅግ የሚያሳዝን ድርጊት እንደሆነ ቃለ አቀባዩዋ ራቪና ሻምዳሳኒ ተናግረዋል።

የአማራ ክልላዊ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በወልዲያ ግጭት ህይወታቸው ያለፈና የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን እንዳረጋገጡ ቃለ አቀባዩዋ በጄኔቫ ባደረጉት ንግግራቸው ጠቅሰዋል። አቶ ገዱ በወልዲያ የተፈፀመውን ግድያ በጥንቃቄ መጣራትና መመርመር እንዳለበት መናገራቸውን ቃለ አቀባዩዋ ጠቅሰው ድርጊቱን የማጣራት ሂደቱ ገለልተኛ እና ፈጣን  መሆን እንዳለበት በማሳሰብ የመብት ጥሰቱን የፈጸሙት አካላት በህግ እንዲቀርቡ መደረግ እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቃለ አቀባዩዋ አሳስበዋል።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ የፀጥታ ሃይሎች ስሜታቸውን እና ራሳቸውን መቆጣጠር መለማመድ እንዳለባቸው በማሳወቅ የሰውን ህይወት ከማጥፋት እንዲሁም ሰውንም ከማቁሰል መቆጠብ እንዳለባቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።  በተጨማሪም ህዝቡ ቅሬታውን ወይም ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ መግለፅ እንዳለበትም ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  ሲገልፁ ተደምጠዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በወልዲያ ከጥምቀት በዓል ማግስት የሚከበረውን የቃና ዘገሊላን በዓል ለማክበር በወጡ የእምነቱ ተከታዮች ላይ የፀጥታ ሃይሎች በከፈቱት ተኩስ በትንሹ 7 ሰዎች መግደላቸውን ቢያሳውቁም የግጭቱን ትክክለኛ መንስኤ ግን ሳይገልፁ መቅረታቸውን ሮይተርስ በዜናው ዘግቧል።