በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ለብዙዎች ህይወት መቀጠፍ እንዲሁም በብዙ መቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል።

ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በሀገሪቱ ተንሰራፍተው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ህይወት መጥፋት እንዲሁም የመማር ማስተማሩን ሂደት ማስተጓጓላቸው ጭምር ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ አመላካች ነው።

በተለይም ከሰሞኑ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ምላሽም የሟቾች ቁጥር እንዲያሻቅብ እንዲሁም ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎችና ትችቶች እንዲያይሉ ምክንያት ሆነዋል።

ከባለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እነዚህ ሀገር አቀፍ ተቃውሞዎች ቢነሱም በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ብዙዎች ይናገራሉ። በተለያዩ ብሔሮችም መካከል ያለው መፈራረቅና መጠላላትም የሀገሪቷ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች እያስነሱ ነው።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግጭት የደረሱ መፈናቀሎችና ሞቶች፣ በተለያዩ ዪኒቨርሲቲዎች ላይ ያጋጠሙ ግጭቶችና የህይወት መጥፋቶች እንዲሁም ተቃውሞችስ በአዲስ አበባ ተፅእኖ መፍጠር ችለው ይሆን? በክልሎች የሚነሱ ጥያቄዎችስ የሀገሪቱ መዲና ነዋሪ ጥያቄዎች ናቸው?

በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የአዲስ አበባን ሕዝብ ማንቀሳስ ችሎ የነበረው ቅንጅት የቀድሞ አባል የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው “አዲስ አበባ ውስጥ ግጭት ላይኖር ይችላል፣ ጥይት ላይተኮስ ይችላል፣ ሰው ላይሞት ይችላል፣ ህዝቡ ግን በውስጡ ሰላም ያለው አይመስለኝም” ይላሉ።

ውጥረቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዳለ የሚገልፁት አቶ ልደቱ አዲስ አባባ የተለያዩ ሕዝቦች መናኸሪያ መሆኗና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ላይ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ብሔርን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው እንደዚህ አይነት ግጭቶች አዲስ አበባ ላይ የመፈጠር ዕድላቸው ኢምንት መሆናቸውንም ይናገራሉ።

“ነገር ግን ከተፈጠረ በጣም አደገኛ ነው፤ ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ይሆናል” በማለት ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
በአፍሪካ የፖለቲካ ፍልስፍና ምሁር የሆኑት ዶክተር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ እነዚህ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች በመከሰታቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሱን የከተማው ነዋሪ ቢያውቁም ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንዳልተገነዘበ ይገልፃሉ።

“የተለመደች አባባል አለች፤ የአዲስ አበባ ልጅ ሰፈር እንጂ ብሔር አይጠየቅም የምትል፤ ምንም እንኳን የብሔርም ይሁን የመደብ ጥያቄ ብዙ አስርት ዓመታትን ቢያስቆጥሩም አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያ በሚለው እንጂ በብሔር ራስን የመግለፅ ነገር የለውም። ስለዚህም እየገጠሙ ላሉት የብሔር ግጭቶች አትኩሮትን ነፍጓል።

ምንም እንኳን አሁን እየታዩ ያሉት ግጭቶች ከማንነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ቢነገርም ሥርዓቱ ላይም እንደ ፍትህ ማጣት፣ የወጣቱ ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትም እንዲሁም ሌሎች ጥያቄዎችም እየተነሱ ነው።
መንግሥት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ማፈንን እንዲሁም ፅንፈኛ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ብዙዎች የሚናገሩ ሲሆን በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉት ከተሞች የመንግሥት የቁጥጥር መዋቅርም ከሌሎች ከተሞች በበለጠ የጠበቀ መሆኑም ይነጋራል።አብዛኛው የፀጥታ ኃይል አዲስ አበባ አለ። የመንግሥት መዋቅር በከተማዋ ስር የሰደደ በመሆኑ ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ መቆጣጠር ይችላል።

በተለይም ከሌሎች ክልሎች በበለጠ በአዲስ አበባ አንድ ለአምስት የሚባለው የገዢው ፓርቲ መዋቅር ስር የሰደደና የማያፈናፍን መሆኑንም ጭምር።

አዲስ አበባ ለዘመናት የከተማ የተቃውሞዎች እንቅስቃሴ መነሻ የነበረች ስትሆን ከዚያም በኋላ ግን ወደ ሌሎች ክልሎች የመዛመት ባህርይ ነበራቸው።

በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንዲሁም በ1997 ዓ.ም ከምርጫ ጋር ተያይዞ የተነሳውም ተቃውሞዎች ተጠቃሽ ናቸው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን በተለያዩ ክልሎች ተቃውሞዎች ቢነሱም በአዲስ አበባ የተደራጀ እንቅስቃሴ አይታይም። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት ቀደም ባሉት ተሞክሮዎች ህብረተሰቡ ውስጥ የነበሩትን እንቅስቃሴዎችን የሚያደረጁትም የሚመሩትም ተቃዋሚዎች ነበሩ።

“ሌሎች ከተሞች ለአዲስ አበባ ድጋፍ ከመስጠት ጋር ተያይዞ ነው የሚቀሰቀሱት አሁን ደግሞ በተቃራኒው ነው።

በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ቀውሶች ወደ አዲስ አበባ ላለመዛመታቸው ምንም አይነት ዋስትና የለም ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ቢቀጣጠል ደግሞ የበለጠ አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

“አሁን እየተከሰቱ ያሉት የብሔር ግጭቶች ከቁጥጥር ውጭ ያልወጡትም ችግሩ አዲስ አበባ ላይ ስላልተከሰተ ነው” ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ይከሰቱ የነበሩት ተቃውሞዎች በሥርዓቱ ላይ ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉት ግጭቶች ቅርፃቸውና ይዘታቸው ተቀይሯ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here