አቅም ያንሰናል ወይ (ከግርማ ቢረጋ)

0

ለምን ዝም ተባለ ወገን
ምንድነው ዝምታው ምንስ እንበል።
የጋምቤላው እልቂት ፊልም መስሎህ ከርሞ፣
አርሲ ላይ ሲቃጠል ዝም ብለኸው ደሞ።

የጎንደር የጎጃም  ህመም ካላመመህ፣
የኦሮሞው ፍጅት ያላንገበገበህ፣
ዝም ስትል ጊዜ ሃዘን ባይሰማህ።

ይኸው ደሞ መጡ ህፃን እየፈጁ፣
ተፈበረከልህ ወንጀል በየፈርጁ።
ወልዲያ ፣መርሳ ፣ ቆቦ አላመጣ ላይ፣
ጀግና ተፈጠረ እኔ አልሞትም ባይ።

እስኪገድሉህ ጠብቅ ሁሉን በየተራ፣
መግደል ይወዳሉ  ብዬ እንዳለወራ፣
ቀድሞ የሰማሁት በታሪክ አሻራ፣
የእንቁላል ቀቃይ ልጅ ተብሎ ሲጠራ።

አልነበሩም ገዳይ ነበሩ እንጂ ባንዳ፣
ግፍ እያቆዩህ ተቀበል ባለ እዳ።
ጥላቻ ተረግዞ ቂም በመወለዱ፣
ጠላሁዋቸው እኔስ ከዚያ  የተወለዱ።

ሕመሙ አያማቸው ችግሩ አይገባቸው፣
ለምን ተብሎ ቢባል ተጠቃሚ ናቸው።
አሊያማ ዝም አይሉም ፀጥታም አይነግስ፣
ሓሳባቸው ባይሆን እንደ አጋሰስ።

ምንም ብኮንነው የእግዜሩን ፍጡር፣
ፀፀት አይገባኝም ከቶ አልሸበር።
ለሆዱ የሚያስብ ተኝቶ ሲነቃ፣
እኔ ብዬዋለው ወያኔ ነው በቃ።

አሁንስ ሁሉም ያማል ምንድነው ነገሩ፣
አቅም ያንሰናል ወይ ለመተባበሩ።
እነሱ ለመግደል ባንድነት ሲቆሙ፣
ለመከላከሉስ የለንም ወይ አቅሙ።

ግራ ቀኙን አይተን መሄድ ካቃተን፣
ምን ይሆን ምክንያቱ ምንስ  አስፈራን።
ጥይት በልብህ ውስጥ ሰርስሮህ እየገባ፣
ለማለት  የማትደፍር ሆድህ የሚባባ።

ምንድን ነኝ ልትል ነው ምንስ ነው ምክንያትህ፣
የሞት ሞት ገስግሶ ሲገባ ከቤትህ፣
ለጋራ ጠላትህ ማበር ካቃተህ፣
ግባ እንጨቆረሬ እዚያ ይሁን ቤትህ።

ጃንዋሪ 2018
ስቶክሆልም / ስዊድን