በወልዲያና በመርሳ የፀጥታ ሃይሎች አላስፈላጊ እርምጃና አፈና እየተጠቀሙ መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

በወልዲያ በቆቦ እና በመርሳ በመንግስት ላይ ተቋውሞ ባሰሙ ህዝቦች ላይ የሚፈፀመው የግድያና የሃይል እርምጃ እንዳልቆመና ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

በመርሳ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱ ከከተማው ከንቲባ አቶ አዲሴ መለሰ ጋር በአዳራሽ ውስጥ ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት በርካታ ወጣቶች ከውጪ ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደነበሩና የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በአስለቃሽ ጭስ ካፈኗቸው በኋላ ፍፁም ኢ ሰብአዊ በሆነ መንገድ በመደብደብ ወደ አልታወቀ ስፍራ እንደወሰዷቸው ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

እነዚህ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሌላቸውና ዜጋ አይመስሉም ያሉት ነዋሪዎቹ ሰውን ከፍተኛ የአካል ጉዳት እስኪደርስበት ድረስ እንደሚደበድቡ ገልፀዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች የታሰሩት ወጣቶች ይፈቱ ሃላፊነቱን እንወስዳለን ቢሉም በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር እንደሆኑና እንደማይለቀቁ ተነግሯቸዋል፡፡

በወልዲያም  ከተማ ሁሉም ነገር ዝግ ሆኖ እንደዋለና ረብሻ ቀስቃሽ ናችሁ የተባሉ ወጣቶችና ባለሃብቶች  እየታፈኑ ወደ አልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ ይገኛል፡፡