በዚህ 27 አመታት ውስጥ  የጅምላ ግድያዎች!! የጅምላ ስደቶች!! በአጠቃላይ በእኛ በኢትዮጵያዊያን ላይ ለማየት የሚዘገንኑ፣ ለመስማት የሚቀፉ እጅግ አሰቃቂና ፍጡራን ሊሸከሟቸው የማይችሉ  በድሎች በተቀነባበረ ሁኔታ በአምባ ገነኑ ስርዓት ተፈጽመውብናል። ዛሬም አላቆሙም። እንዲያውም በይአነትም፣በመጠንም ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሰላም አውለኝ ብሎ በሰላም የማይዋልበት፣በሰላም መግባበት የማይቻልበት!! አልሞ ተኳሽ ከየትኛው ፎቅ ወይም የትኛውን ከለላና መከታ ተጥቅሞ ግባርህን ብሎ እንደሚጥልህ የማታውቅበት ሁኔታ ተፈጥረዋል። ብዙዎች እንደሚሉት አገራችን ‘በመንግስታዊ ሽብር’ እየተናጠች ትገኛለች።

የሩቁ ይቅርብንና በሃገራችን ሁለት ዓመታትን ባሳለፈው፣ መነሻውን ኦሮሚያ ጊጭ ላይ አድርጎ በህዳር 2008 ዓ.ም ተጀምሮ፣ በአንዴ መላው ኦሮሚያን  አጥለቅልቆ እንደ ሰደድ እሳት በመዛመት አብዛኛውን የአገራችንን ክፍል ሸፍኖ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ህዝብ ምሬቱንና ብሶቱን በአገዛዙ ላይ በማሰማቱ ብቻ ከህጻን እስከ አዛውንት ድረስ አገዛዙ የጅምላ ፍጂት ፈጽሟል።የነገ ሃገር ተረካቢ ህጻናት ደብተራቸውን በጉያቸው ወሽቀው እውቀት ለመቅሰም ወደ ትምህርት ቤት እየተጓዙ በነበረበት ቅጽበት በአጋዚ ጥይት  ጭንቅላታቸው ተገምሶ ደማቸው እንደ ጎርፍ ፈሶ፣አጥንታቸው ተከስክሶ መንገድ ላይ  ወድቀው እንደወጡ ቀርተዋል።

ልጇን ዘጠኝ ወር በሆዷ ተሸክማ፣ አምጣ የወለደች እናት የእቦቀቅላ ህጻኗ ጭንቅላት በስናይፐር ጥይት ተገምሶ ስታይ ምን ይሰማት ይሆን? ስሜቱን ለመጋራት ሞክራችሁና ጥረት አድርጋችሁ ታውቃላችሁን? ልጇን በጭካኔ ገለው ከልጇ አስከሬን ላይ ተቀመጭ የተባለች ምስኪን እናት የሃዘኑን ክብደት እንዴት ተሸክማው ይሆን? ሁላችንም እስቲ የእናቶቻችን ስሜት ለመጋራት እንሞክር።ይህን ጭካኔ  ከሰው ልጅ አብራክ ተገኝቶ ሰው የሆነ ሁሉ እንዴት በሰው ላይ ለመፈጸም ይቻለዋል?

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት በአገራችን እያደረሳቸው ያሉ ፈርጀ ብዙ በደሎች ተቆጥረውም፣ተሰፍረውም አያልቁም። የእምነት በአላትን እንኳን በሰላም ማክበር አልተቻለም። አምና በ2009 ዓ.ም በደብረዘይት ቢሸፍቱ ሃይቅ አመታዊው የእሬቻ በአል ሲከበር ከ600 በላይ ምእመናን አምላካቸውን ለማመስገን ከየሰፈራቸው ተጠራርተው የወጡ ሳይመለሱ እንደወጡ ቀርተዋል። የዛሬ ዓመት በሰላም አድርሰን ብለው ወደሰማይ አንጋጠው ለፈጣሪያቸው ጸሎት ያቀረቡ፣ እንኳን ለአመቱ ሊደርሱ ከቤታቸውም መመለስ ሳይችሉ በዋሉበት በጥይት አር ነደውና ተቃጥለው ቀርተዋል። በዚህም ልባችን በሃዘን ጦር ተወግቶ ቷል። እጅግ የሚያበሳጨው ደግሞ የደደቢቱ ወያኔ ወገኖቻችንን  በግፍ ከፈጀ በኋላ  የሶት ቀናት ሃዘን  ብሎ በመላ ሃገሪቱ ማወጁ እና ለጨፈጨፋቸው ሃውልት ማቆሙ ነው። ‘የአዞ እንባ’ ይሉሃል ይሄነው። ህወሃት በአንድ እጁ ቃታ ስቦ ህዝብን እየረፈረፈ፣ በሌላ እጁ ደግሞ የሃዘን መግለጫ ያወጣል። ‘ይውጋህ ብሎ ይማርህ’ በሚሉት ብሂል ላለፉት 26 ዓመታት እየታለለ በህዝባችን ላይ የእልቂት መብረቅ አውርዶበታል።

እናም አምና በሪቻ በአል የተፈጸመው ግፍ ዘንድሮም ወልዲያ ላይ ተደግሟል። እጅግ  የሚገርመው ደግሞ አገዛዙ በየመግለጫው ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ሃላፊነት እወስዳለሁ ብሎ  ይቅርታ በጠየቀበት <<ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ስል. . .>> የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ብሎ ቃል በገባበትና ህዝብ ቃሉን ያከብር ይሆን ብሎ በጥርጣሬ እየተመለከተ ባለበት ማግስት መሆኑ ነው።በእርግጥ ህወሃት ለሃገርና ለውገን አስቦ እንደማያውቅ ሃቅ ነው። ሁሌም ቢሆን ፖለቲካዊ ስሌቱ ነው የሚያስቀድመው። በየቦታው ተቃዉሞዎች በርከት በማለታቸው ምክንያትና ግባተ-ቀብሩ ሊፈጸም እደሚሆን ካወቀ፣ ህዝብን አታሎና ለስለስ ብሎ ይቀርባል። በመሆኑም የዘንድሮው የህወሃት ይቅርታ መጠየቅም ሆነ፣ ጥቂት እስረኞችን ከእስር መለቀቅ ምክንያት የቆሰለው ቁስል ሽሮ እስከሚያንሰራራ ድረስ ነበር። ለዚህም ነው መልሶ መቋቋም አድርጎ በወልድያ ህዝብ ላይ ቂሙን የተወጣው።

በህዳር ወር በመቀሌ ከተማ እግርኳስ ክለብና በወልድያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ መካከል ወልድያ ላይ በተደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ፣ ህወሃት ከመቀሌ እግር ኳስን ለመደገፍ ሳይሆን ለጠብ አጫሪነት አስልጥኖ ባመጣቸው አባላቱ አማካኝነት በህዝቡ ላይ በተሰነዘረው ጸያፍና ጠብ አጫሪ ስድብ ምክንያት ግጭት ተፈጥሮ የሰው ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል። በወቅቱ ወገኖቹን በአጋዚ ጥይት ለዘላለሙ የተነጠቀው የወልድያ ህዝብም፣ በዘር መሰረታቸው  ሳይሆን የስርዓቱ አገልጋይ በመሆን እና የአካባቢዊን ህዝብ እየጠቆሙ በሚያሳፍኑ ብቻ ሳይሆን  በሚያፍኑ፣በዘረፋ በተከማቹ የግለሰብ ባልሆኑ ግን <<የግለሰብ>> ንብረቶች በተባሉ ላይ ህዝቡ የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ አይዘነጋም። ግን ህወህት በጌዜው  ከፈጀው የውልድያ ወጣት ህይወት በላይ ያንገበገብው የአባላቱ ንብረት መውደም በመሆኑ ቂሙን በልቡ አምቆ እንሆ ጊዜ ሲጠብቅ ቆየ። ግን ብዙ አልጠበቀም። የወጣቱን ደም ዳግም እደጎርፍ የሚጎርፍበት ቀን አገኘ።

ጥር 12 የሚውለውን ዓመታዊውን የሚካኤል በል ምክንያት በማድረግና ታቦተ-ህጉን በእልልታ፣በሆታ  ለማጀብ፣ለመከብከብ በወጡ ወጣቶች በቃና ዘገሊላ እለት ውሃውን ወደ ወይን በቀየረበት ቀን ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የወልዲያን ወጣቶች በሚካኤል ጽላት ፊት. . .ለፊት ደማቸውን እደውሃ አፈሰሰው። የወልድያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የሚካኤልንም ታቦት ክብርም ተገረሰሰ!! አገራችን ውስጥ እምነትህን በነጻነት ማራመድ የለም።ስለ እምነታቸው የተከራከሩ የዋልድባ መነኮሳት፣የምንኩስና ቆባቸው ወልቆ ተገልብጠው እየተገረፉ ነው።

በጥምቀት እለት በወልድያ ህዝብ ላይ የተፈጸመው የጭካኔ እርምጃ ያስቆጣው የወገኑ ደም መፍሰስ የጠዘጠዘው የቆቦ፣ የመርሳ ህዝብ ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት ተቃሞውን ተቀላቅሏል። መኖር ካለብኝም ከወገኔ ጋር መሞት ካለብኝም መቃብሬ አብሮይሁን ብሏል። አገዛዙ በታላቁ የእምነት በአል በጥምቀት እለት በወሎ ህዝብ ላይ የሳበውን ቃታ ጥብቁን አልዘጋውም።አሁን በሩምታተኩስ ሰውን እየፈጀ ነው።

በነገራችን ላይ  በሃገራችን ስለ እምነት ነጻነት ህገ-መንግስቱ ላይ ብቻ ነው ያለው። ህወሃት <<አቻ የማይገኝለት>> እያለ የሚመጻደቅበትን ህገ-መንግስት እንኳን ራሱ በተደጋጋሚ ሲገረስሰው ተመልክተናል። ነገርግን በየጊዜው የሚጥሰውን ህገመንግስት ሌሎች እንዲያከብሩለት ይጠይቃል። ሲቀጥልም ሃሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ የሞከሩትን ጋዜጠኞችና  የመደራጀት መብታቸውን በመጠቀም ማቸው የተነሳ የፖላቲካ ፓርቲ አባላት <<ህገ-መንግስታዊ ስረቱን ለመናድ>> በሚል የቅጥፈት ክስ በመለጠፍ ህወሃት እራሱ ከሳሽ፣እራሱ ምስካሪ፣እራሱ ዳኛ በመሆን ወደ ማይጠረቃው ወህኒ ቤት በእየጊዜው ሲያወርዳቸው ተመክተናል። የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን፣ መንግስት በእምነታችን ጣልቃ አትግባብን ስላሉ እና እባክህ በብቸኝነት አርቅቀህና አጽደቀህ የጫንክብነን ህገ-መንግስታዊ መብታችን አክበርልን በማለታቸው ምክንያት ብቻ እጅግ በብዙዎች ላይ የጭካኔ እርምጃ መወሰዱን መቼም ቢሆን አንዘነጋውም።

ታዲያ እስከ መቼ ነው ወገን እያለቀ ፣ጉድጓድ ቆፍሮ መቅበር የማይሰለቸው? እስከመቸ ነው ድንኳን መትከል መንቀል፣የማያንገሸግሸው? ወገኖቻችንን በእየጌዜው እየቀበርን እንዴት ብሎ በአይናችን እንቅልፍ ይዞራል? እስከመቼ ነው በህወሃት እየተታለሉና እየተደፈጠጡ መሞት የሚያቆመው? እስከመቼነው ዘመዶቻችን እየተሰደዱ መንገድ ላይ ገላቸው እየተበለተ ለሽያጭ እየቀረበ የሚዘልቀው? እስከመቼ ነው ልክ በ15ኛው  መቶ ክፍለዘመን እንደነበረው የባሪያ ሽያጭ ዛሬም በሊቢያና በተለያዩ የአረብ አገራቶች ወገኞቻችን እንደ እቃ እየተሸጡ፣እየተለውጡ የሚቀጥሉት?

እውነት. . .እውነት. . . እንልህ አለን ካልመረክና ካልቆረጥክ እናም አምባገነኑና ሰው በላውን አገዛዝ ጨክነህ ታግለህ ካልገነደስክ፣ትናት የእቦቀቅላዋን የሚጡየን አስከሬን በክንድህ ታቅፈህ ወስደህ፣ ጉድጓድ ቆፍረህ እንደ ቀበርክ ሁሉ፣ ዛሬ አንተ ሞትህን ቆመህ እየጠበክ መሆኑን ልናስታውስህ እንወዳለን።  በአጋዚ ጥይት ግባርህን ተብለህ ወደ ከርሰ መቃብር ወራጅ ተረኛው አንተ መሆንህን ለፍታም ቢሆንም እዳትዘነጋ!!

<<ኧረ ምረር. . .ምረር. . .ምረር እንደ ቅል
ባለመምረሩ ነው ዱባ ሚቀቀል>