ኢትዮጵያ ከቻይና በመቀጠል የኢንተርኔት ገደብ በመጣል ከአለም ሁለተኛ ተባለች

አባይ ሚዲያ ዜና
በአሰግድ ታመነ

ፍሪደም ሐውስ፣ ኢትዮጵያ ከቻይና ተከትላ ከሶሪያ እኩል የኢንተርኔት እና የሞባይል ተጠቃሚዎች ላይ ገደቦችን በመጣል በዓለም ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች አለ።

የኢትዮጵያ መንግስት በተከታታይ በተነሳበት ህዝባዊ ተቃውሞ በመደናገጥ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ችግሩን መፍታት ስለተሳነው ህዝባዊ ንቅናቄው ከዳር እስከዳር ተጋግሎ መቀጠሉ ይነገራል። በዚህም የተነሳ አገዛዙ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው የኢንተርኔት አገልግሎት በአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ማቋረጡ ሲነገር በኦሮሚያም የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ከባድ እንደሆነባቸው ነው የሚነገረው። እንደዚሁም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባም አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስቸግር የታወቀ ሲሆን ባጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝና እንዳይለዋወጥ በማድረግ ተቃውሞውን በሃይል ለመጨፍለቅ እየሞከረ መሆኑን ይነገራል።

ሀገሪቷ በፖለቲካ ምክንያት ኢንተርኔት ስታቋርጥ ለመጀመርያ ጊዜ አለመሆኑን አዲስ እስታንዳርድ ዘግቧል። ጋዜጣው እንደዘገበው ከሆነ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ኢንተርኔት መጠቀም ከባድ ነው ብሏል። ኢትዮጵያ በድረገጽ ነፃነት ‘Freedom of the Net’  ሪፖርት “የኢንተርኔት ነጻነት የሌለባት እንዲሁም 100% የኢንተርኔት ነጻነት የሌለበት” በሚል መስፈርት ተመዝና 86 ነጥቦችን በማምጣት ከሶሪያ እኩል ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ከቻይና ቀጥላ ተቀምጣለች ብሏል።