እኔ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የአርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ (በታድሎ ደሴ)

ብዙ የአለም ሀገሮች ታላቅ ደረጃ ያደረሷቸው ፣ አባታችን እያሉ የሚጠሯቸው መሪዎች አሏቸው።ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ አሰቃቂ አገዛዝ ያወጣቸውን ኔልሰን ማንዴላን “ማዲባ” ሲሉ በአባትነት ክብር ይጠሩታል። ህንዳውያን ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ያወጣቸውን ማህተመ ጋንዲን እንዲሁ በፍቅርና በጥበብ ተምሳሌትነት ህያው ያደርጉታል። ማሃተመ ማለት አዋቂ፣ የተከበረ፣ ጥበበኛ፣ ሊቅ፣ መምህር ማለት ነው። ቻይናውያን ማኦ ዜዱንግን የዕውነተኛ ኮሚኒስት አባት ይሏቸዋል ። ይህ የሚያሳየን ሕዝቦች በታሪክ ሂደት ውስጥ የሚገጥሟቸውን ችግሮች የፈቱላቸውንና ዘላቂና አስተማማኝ የሰላምና የዕድገት መሰረትን ጥለው ያለፉ ቀደምቶቻቸውን በጽሁፍ፣ በአፈታሪክ፣ በጨዋታ፣ በተረትና በተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቻቸው እንደሚያሞግሷቸው፣ እንደሚዘክሯቸውና ባለውለታነታቸውን እንደሚመሰክሩላቸው ያሳየናል። እነኚህ ግለሰቦች ባጭሩ የህዝብና የሃገር አባት ተብለው ይጠራሉ።

ይህ ዕውነት ደግም በኛዋ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ዘንድም የሚሰራበት ክስተት ነው። ጥንታዊና ዘመናዊ ኢትዮጵያን በመወጠኑና በመቅረጹ ረገድ ከነችግሮቻቸውም ቢሆን ብዙ የለፉና የታገሉ ባለውለታዎች ነበሩን፣ አሁንም አሉን። አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ዮሀንስ፣ ራስ ጎበና፣ አጼ ሚኒሊክ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።እነሱ የሚችሉትን ሁሉ አድርገው አልፈዋል። ዕውቅና፣ ክብርና ቦታ መስጠቱ የኛ የተከታዮቻቸው ሃላፊነት ይሆናል  ማለት ነው።

ዛሬ ከነኚህ ባለውለታዎቻችን ተርታ ስማቸውን ልናነሳ የፈለግነው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ነው። ለዚህ ክብርና ቦታ የግለሰቡ ሰማዕት መሆን ወይንም በህይወት ኣለመኖር የግድ አይደለም። እናም ትንሽ ስለፕሮፌሰር ብርሃኑ ልንናገር ወደድን።

ከታዋቂው የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅ አንዳርጋቸው ጽጌና ከሌሎች ጥቂት ግለሰቦች ጋር በመሆን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ያቋቋሙት ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ በስትራቴጂያዊው ሁለገብ የትግል ስልቱ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህወሃት አገዛዝ ህልውና ትልቅ ስጋት የሆነ ድርጅት መሆኑን አስመስክሯል። ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ጋር ከተዋሃደና አርበኞች ግንቦት 7 ከሆነ ወዲህም  የህዝባዊ እንቢተኝነት እና የትጥቅ ትግልን በአንድ ላይ አጣምሮ በማራመድ እጅግ ታላቅ ስኬት ያስመዘገበና በአብዛኛው ኢትዮጵያውያዊ ዘንድ አገራችንን ለመታደግ ተስፋ የሚጣልበት ድርጅት መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው ። ለዚህ ስኬት ትልቁንና ቀዳሚውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ደግሞ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተመቻቸ ሕይወታቸውን ላገራቸውና ለህዝባቸው ሲሉ መስዋዕት ያደረጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው።

ፕሮፌሰሩና የሚመሩት ድርጅት ለምን ታላቅ እምነት ተጣለባቸው የሚለው ጥያቄ ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሼ እንዳስብበት ያስገድደኛል። እኔ ዕድሜዬ በ20ዎቹ መጨረሻ ላይ ያለሁ ወጣት ነኝ። ስለፕሮፌሰር ብርሃኑ የገዘፈ ስብዕና እንዲኖረኝ ያደረጉት ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜ መምህራኖቼ  ግለሰቡ የተለየ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዳላቸውና ህዝባቸውንም ከተጋረጠበት የኑሮ ፈተና እንዲያልፍ ትልቅ ስራ ለመስራት ቆርጠው የተነሱ ምሁር መሆናቸውን አስተምረውኛል። አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት የወያኔው ፍርድ ቤት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን በሽብር ወንጀል ከሶ በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት መፍረዱን በሬዲዮ ሲያውጅ አሁን ለደህንነቷ ስል ስሟን የማልጠቅሳት መምህሬ “ታላቁ የዚህች ሀገር የነፃነት አባት የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው እየሰማሁ በሰላም ማስተማር አልችልም ተማሪዎቼ ይቅርታ አድርጉልኝ”ብላ ዕምባና ሳግ እየተናነቃት ክፍሉን ጥላ እንደወጣች አስታውሳለሁ። ከዝች ቀን በኋላ ፕሮፌሰርን በአካል ለማግኘት በጣም ፈለግኩ። በእርሱ መማር ተመኘዉ፣ለምንስ የነጸነት አባት እያሉ ብዙ የቀድሞ ተማሪዎቹ መሰከሩለት የሚሉት ጥያቄዎች ያልተፈቱ እንቆቅልሾች ሆኑብኝ። ይህን እንቆቅልሽ ለመፍታት ያለኝ ቁርጠኝነት በውስጤ እያየለ ሲመጣ ይታወቀኛል። ሆኖም ወያኔ እስካለ ድረስ ይህ ምኞት ከንቱ ቅዠት ሆኖ እንደሚቀር እገምት ነበር። እናም የዩንቨርስቲ ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ  በወያኔ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሬ ለሶስት አመት አገለገልኩና ከሆዴና ነጻነቴ መምረጥ የግድ የነበረበት ወቅት ላይ ደረስኩ። ብዙ ኢትዮጵያዊያን አገዛዙን ከልባቸው እንደሚጠሉ አውቃለሁ። ዘረኝነቱና አድሏዋዊነቱ እያንገፈገፋቸውም ቢሆን በብዙ ነገሮች በተለይም ከቤተሰብ ጋር በተገናኙ ምክንያቶች የተነሳ አንገታቸውን ደፍተው፣ በዝምታ ኑሮአቸውን እንደሚገፉ በቅርብ ተከታትያለሁ። እኔ ገና ወጣት ነኝ፣እናም አንጻራዊ ነጻነቱ ነበረኝ። ለሆዴ፣ ለሚስትና ለልጆቼ የምለው ነገር አልነበረኝምና ስራዬን ለቅቄ የነፃነት አባቴ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ፍለጋ ወደ ኤርትራ በርሃ ወረድኩ።ብዙም ሳልቆይ ከአርበኞች ግንቦት 7 የነጻነት ተፋላሚዎች ጋር ሆነው በአካል አገኘኋቸው። የተሰማኝን ስሜት ለመግለጽ አልችልም።  አንገታቸው ላይ ተጠምጥሜ እንቅ አድርጌ ሳምኳቸው።  መች በቀላሉ ለቀቅኳቸውና።  ደግነቱ ግን የወያኔ ፖሊስ ወይንም ባለስልጣን ባለመኖሩ እንጂ እንደነመረራ ጉዲና ወደ ቃሊቲ ከመወርወር አልድንም ነበር። ሕገ-መንግስቱ ከአሸባሪዎች ጋር ሻይ ቡና የጠጣም ቢሆን አይማርም ይላልና የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል በድርጅቱ አባላትና አመራሮች ከተደረገልኝ በኋላ እንዳንድ ጭውውቶችን ከፕሮፌሰር ጋር ጀመርን። የምሰማውና የማየው ነገር ግን ካሁን በፊት ስለ እሳቸዉ ከማውቀውና ከሰማሁት በላይ ሆነብኝ።በተለይም ልዩ ስሜት የፈጠረብኝ ትእይንት አርበኞቹ በሙሉ ለሳቸው የሚያሳዩዋቸው አክብሮትና ፍቅር ነበር። አብዛኛውን አርበኛ በስም እየጠሩ ሲያናግሩ፣ ሁሉንም በሙሉ ትኩረት ሲያስተናግዱ፣ ጥያቄዎችን በተረጋጋና በግልጽነት ሲመልሱና ሲያስረዱ፣ ውስብስብ የሆነውን ያለማችንን ፖለቲካ ቀለል ባለ አማርኛ ሲተነትኑና፣ ንቅናቄአችን አርበኞች ግንቦት 7 የቆመላቸውን የዲሞክራሲ፣የፍትህና የእኩልነት መርሆዎች እንደንጹህ የምንጭ ውሃ ጥርት ባለ ቋንቋ ሲያሰርፁ ሳይ በውነትም የኢትዮጲያ ህዝብ ለኚህ ሰው ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ቢያሳያቸው ዕውነት ነው ስል ደመደምኩ። በልቤም በስእብናቸው፣ በአመራር ችሎታቸው፣ በረዥም ጊዜ ራዕያቸውና ምሁራዊ አንደበታቸው ትልቅ ዕውቅናን ከተጎናጸፉ ጥቂት የአለማችን ኮከቦች ጋር አወዳደርኳቸው። የኢትዮጵያንና የህዝቧን ስቃይ ካራዘሙት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛ የምሁራኖቻችን ቸልተኝነትና አንዳንዴም አድርባይነት መሆኑን ሳስብ ምን ነበረበት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ትንሽ ቢማሩ እላለሁ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ማለት በወያኔ/ህወሃት ዘመን በጨለመው የኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ደምቀው የሚታዩና አቅጣጫን ጠቋሚ የሆኑ የሰሜን ኮከብ ናቸው።

ለመግቢያ ያክል ይህን ካልኩ በኋላ በትንሹም ቢሆን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ላይ ያየኋችው የተለዩ ሁኔታዎችን እና ድርጅታቸው አርበኞች ግንቦት ሰባትን  በተመለከተ ትንሽ ልናገር። ፕሮፌሰር ብርሃኑን መሪዬ ናቸው ብዬ የተቀበልኩባቸው ዋና ዋና ምክንያቶቼ

           የሀገራቸውን ፖለቲካ ከስር መሰረቱ ጠንቅቀው ከማንም በላይ ማወቃቸው።

           የዕውቀት እና የትምህርት ችሎታቸዉ እጅግ የዳበረና  ከፍተኛ የራስ መተማመን ያላቸው በመሆኑ።

          ለሰው ልጅ ሁሌም ስኬትን እንጅ ዉድቀትን የማይመኙ፣ ወደ ኋላ ጎታች የሆኑ መጥፎ ባህላዊም ሆኑ ዘመናዊ እሴቶችን በእጅጉ                የሚጠየፉ በመሆናቸው።

          ሁሌም በውይይትና በንግግር የሚያምኑ፣ ከማንም ጋር ሀገርን የሚጠቅም ጉዳይ እስከሆነ ድረስ አብሮ ለመስራት የተለየ ቁርጠኝነት፣            ቀናነትና አብሮ የመስራት ችሎታ ያላቸው በመሆናቸዉ።

          ከግል ጥቅም ይልቅ የህዝብን ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸው

          በዚህ አለም ውስጥ ከነጻነት በላይ ምንም ሌላ የከበረ ነገር እንደሌለ የተረዱ መሆናቸው

          ደፋርና ቆራጥ፣ ሃሞተ ኮስታራ የሆኑ ፣ ብዙዎች ምድራዊ ገነት ከሚሏት አሜሪካ  በቀጥታ በርሃ የወረዱ ታጋይ መሆናቸው።

         ከወያኔ ጋር ሙሉ ለሙሉ የተቆራረጡና መወገድ እንዳለበት ቀድመው በመረዳታቸዉ ከሰላማዊ ትግል እኩል የነፍጥ ትግል                     አስፈላጊነቱን  አምነው ሁለንተናዊ የትግል ስትራቴጂ የነደፉ ስለሆኑ።

የድርጅታቸው አላማ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል በዜግነት ላይ የተመሰረተ ተጠቃሚነትን የሚያራምድና ሰው መጀመሪያ በሰውነቱ ከዛም ደግሞ በኢትዮጵያዊነቱ ወይንም በኢትዮጲያዊነቷ እንጅ በዘር፣ በቋንቋ፣ በብሄርና በዕምነት የሚለካ አለመሆኑን ከልብ ማመናቸውና ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፈል ሲሞከርም ሓገራዊ ቁስል ሆኖ የሚያማቸው በመሆናቸው።

ለሰዉ ለጅ ህይወት ታላቅ ዋጋ የሚሰጡ፣ አንድ ግለሰብ አለምን መለወጥ እንደሚችል የሚያምኑና የእያንዳንዱ ሰው ህይወት ትልቅ ዋጋ ያለው በመሆኑ የሚመሩት ትግል ደምና አጥንትን የሚጠይቅ ቢሆንም በተቻላቸው መጠን ይህንን ዋጋ ለመቀነስ  የሚጥሩ መሆናቸው በእስካሁኑ የበረሃ ቆይታዬ ተረድቻለሁ።

 በነዚህ ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች የተነሳም እኔ እንደ አንድ የነጻነት ታጋይና ኢትዮጵያዊያንም በሙሉ በዘመናዊ ያገራችን ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትክክለኛ የሆኑ መሪ ኢትዮጵያ ስለማግኘቷ ምንም አይነት ጥርጣሬ እንደሌለኝ የዐይን ምስክር መሆን እችላለሁ። ከጎናቸውም ሆኜ ለዚህ ልዩ ዕድል በመብቃቴም ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ። ከኚህ ጀግና ጋርም በትግል አውድ ላይ ባንድነት ብሰዋ ለኔ ትልቅ ክብርና ሞገስ ይሆንልኛል።

የአርበኞች ግንቦት 7  ራዕይ እንዲህ ይላል ፦ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊና ሰባዓዊ መብቱ የተከበረባት ፣የኢኮኖሚ ብልጽግናና ማህበራዊ ፍትህ የሚገኝባት ፣የዜጎች ህይወት ፣ደህንነትና ጥቅም የተከበረባት እና የህዝቦቿ አንድነትና ትስስር የጠነከረባት ሀገር ኖሮት ማየት ነው”ይላል።

አርበኞች ግንቦት 7 ተልዕኮን ሲያስቀምጥም ፦የመንግስትና የፖለቲካ ስልጣን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበት ፣የሀገሪቱ የዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለጥበት ፣ማህበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለጽግበት ብሔራዊ የፖለቲካ ስርዓት እንዲገነባ ማገዝ ነው።

                                 ግቦቹ ሁለት ዋና ዋና ሲሆኑ

  1. ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ የሕዝብ ምርጫ ብቻ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበት ስርዓት ማስጀመር ።
  2. ሰላማዊ፣ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስልጣን አያያዝ ሂደት ብልጭ ብሎ እንደገና በአንባገነኖች ግርሻ መልሶ እንዳይጠፋ ጠንካራ መሰረት ያለዉ የዲሞክራሲ ተቋማትንና ባህልን መገንባት የሚሉ ሲሆኑ 6 መለስተኛ ግቦችም አሉት። እነኚህን የቀሩትን ዝርዝሮች እንድታነቡት እየጋበዝኩ ፕሮፌሰር ብርሃኑና ድርጅታቸው አርበኞች ግንቦት ሰባት የኢትዮጵያውያንን የዘላለም የጨለማ መሰናክሎች በማስወገድ ወደ ብርሃን ማማዉ በከፈተኛ ፍጥነት እየተጓዙ ነውና እርስዎም የነፃነቱን ሻማ ለኩሰው አብረው እልህ አስጨራሹን ጉዞ እንዲጓዙ መልዕክቴን አስተላልፋለዉ ።

                            ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

                             አንድነት ሃይል ነው!!!