አንተ ወዶ ገዳይ (በወንድምአገኝ አዲስ)

0

አንተ ወዶ ገዳይ፣ የሌለህ አምሳያ፣
አንተ ፈቅዶ ሎሌ፣ አንተ ፈቅዶ ባሪያ።

አንት አነጣጣሪ፣
ተኩሶ ሰባሪ።
አልሞ ተኳሹ፣
ወላድ አስለቃሹ፣
ካፊሩ ሹምባሹ፣
መንፈሰ ድንቡሹ።

አንተ አዎን አንተ፣አንተ ባለ ስናይፐር፣ አጋዚ የሚሉህ፣
እስኪ ልጠይቅህ፣ አንድ ቀን እንደሰው፣ አስበህ ታቃለህ?
ባንዳ ልትታደግ፣ ሌባ ልትጠብቅ፣ የምትባዝነው፣
ሌባ ጣትክን አዘህ፣ እርሳስ ልትዘራ፣ ቃታ ምትጨቁነው።
አንተ ካኪ ለባሽ፣ ባለ ቀይ ቆቡ፣ ያፈሰስከው ቀይ ደም፣
ይታይሀል ከቶ፣ ሊሞግትህ ተግቶ፣ ፊት ለፊትህ ሲቆም።

በለኝ ታዝዤ ነው፣
በለኝ እንጀራ ነው።
ሌላ ምን መልስ አለህ፣
መቼም ለከት የለህ።
እውነት ነው፣ ታዘህ ነው፣

ሎሌ ሆኖ መግደል፣ ላንተ አርበኝነት ነው፣
ከርስህ ሀይማኖትህ፣ ጌታህ አምላክህ ነው።
አውቃለሁ አምናለሁ፣ እስከ ሞላ ሆድህ፣
ትስባለህ ምላጭ፣ አይሞቅህ አይበርድህ።
ትጫናለህ ምላጭ፣ ታወርዳለህ መአት፣
ትቀጫለህ ጨቅላ፣ ትቀጥፋለህ ወጣት፣ ታዘንባለህ እሳት።

አዎን እንጀራ ነው፣ መግደል ክቡር ስራ፣
ላንተ አይነቱ ስንኝ፣ ላንተ ብጤው ሞራ።
ሬሳ መከመር፣ ደም ማፍሰስ በከንቱ፣
ትእዛዝ መፈፀም ነው፣ ደሞም ፋይዳ ለከርስ፣ ላንተ አይነቱ ገልቱ።

ሲሻው ወገን ይለቅ፣ ሲሻት አገር ትጥፋ፣
ከርስ ከሚጎድል፣ጌታ ከሚከፋ፣
የውስጡ አንበሳ፣
የውጭው ሬሳ።

አስቦ ገዳዩ፣  ባለመትረይሱ፣
አባ መግደል ምሱ።
በንፁህ ዜጎች ደም፣ የጨቀየች ነብስህ፣
አጋዚ፣ ፌደራል፣ ልዩ ሀይል የሚሉህ።

ሙክቱ ቅጥቅጡ፣
መንፈሰ ልሙጡ።
ስማ ልጠይቅህ፣ አንተ ያልታደልከው፣
እስኪ አሁን ዮሴፍን፣ ምን ብለህ ጎመድከው?
እስኪ ምን በደለ፣ ባረር የጠበስከው?
ዮሴፍ እኮ ገና፣  ራእይ የነበረው፣
የ14 አመት አመት ልጅ፣ የሀገር የወገን ፣የወላጅ ተስፋ ነው።
ቀድሞ ነገር ቃታው፣ እንዴት ተሳበልህ?
ይህ አንድ ፍሬ ልጅ፣ እንዴት ታለመልህ?

ቅልቡ ወጠምሻ፣ አንተ ፌደራሉ፣
ደም ያንከለከለህ፣ አጋዚው ወደሉ፣
ከቶ ማይታይህ፣ ሳሩ እንጂ ገደሉ።
አንተ ገሎ አዳሪ፣ አንተ ተኩሶ አደር፣
አጋዚ ተብዬ፣ተብዩ ፌደራል።

አነጣጥሮ ጣዩ፣
ግብዙ ገዳዩ።
ያገር የወገን ግፍ፣ ገና ያኝክሀል፣
ከጌቶችህ ጋራ፣ ይቀረጥፍሀል።