የኤችአር 128 ልዑካን ቡድን የሰኞው ድርድር ውጤት ማምጣቱንና ለኢትዮጵያ መንግሥትም የ28 ቀን ገደብ መሰጠቱን ተናገሩ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
ግርማ ቢረጋ

ሰኞ ጃንዋሪ  29 ቀን 2018 የተደረገውን የኤችአር 128 የኢትዮጵያውያን ጉዳይ የሚመለከተው ረቂቀ ሕግ ወደ ምክር ቤት ቀርቦ ድምፅ እንዲሰጥበት በሚል የኢትዮጵያን አሜሪካውያን ከኬቨን ማካርቲ እና በርከት ካሉ የህግ አውጪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

እንደሚታወሰው በውይይታቸው ለኢትዮጵያ መንግሥት የ15 ቀን ገደብ መሰጠቱን ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ የቡድኑ አስተባባሪ በእለቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መናገራቸው የሚታወስ ነው ።

ይሁን እንጂ ይህን ተከትሎ የብዙሃኑ መሪ ኬቨን ማካርቲ ለኤችአር 128 ልዑካን ቡድን ትናንት በላኩት ደብዳቤ ይህ የጊዜ ገደብ ተራዝሞ  የኢትዮጵያ መንግሥት እስክር ፌብርዋሪ 28, 2018  አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ ረቂቅ ሕጉን እንደሚያቀርቡት አረጋግጠዋል። ይህንንም ለኢትዮጵያ መንግሥት ማሳወቃቸውን ጨምረው ኬቨን ማካርቲ  ገልፀዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ሰብሳቢና መስራች ስለ ጉዳዩ ጠይቀናቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተውናል

”ጉዳዩ በዚህ ፍጥነት መሰማቱና  የተከበሩ ኬቨን ማካርቲ የኢትዮጵያውያንን  ድምፅ ሰምተው አስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ማድነቅ እፈልጋለው” ካሉ በኋላ ለኬቨን ማካርቲ ደብዳቤ በመላክ የፈብርዋሪ  28, 2018ን ገደብ ካውንስሉ እንደተቀበለው መልሰን ገልፀንላቸዋል ብለዋል። ይህ ትልቅ ድል ነው ሲሉም አክለው ገልፀዋል ።

የ27 ዓመት  የኢትዮጵያ እናቶች እንባ ሊሰማ የቀሩት ጥቂት ቀናቶች ናቸው እና አይዟችሁ ሲሉ  ተናግረዋል። በተጨማሪም ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ”ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን በማጠናከር የጀመርነውን የዲፕሎማሲ ትግል መቀጠል አለብን። ይህ የሆነው በሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ርብርብ ነው” ብለዋል።

አሁንም እሩጫችን ተጀመረ እንጂ አልተጨረሰም ያሉት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ስልክ በመደወል ኬቨን ማካርቲን ማመሰገን እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ይህንን ጉዳይ በመላ አሜሪካ ለሚደረገው ዘመቻ የኢትዮጵያ አድቮካሲ ኔትወርክን በማግኘት ንቁ ተሳታፊ እንድንሆንም አደራ ብለዋል።