የጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት ማቆሙ ተገለፀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

በአገሪቷ  ግንባር ቀደም የሆነው የጥቁር አንበሳ እስፔሻላይዝ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና አገልግሎት የልብስ ማጠቢያ ማሽን በመበላሸቱ  ምክንያት እየሰጠ የነበረውን የህክምና አገልግሎት ማቆሙ ታወቀ።

በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ይሰጣችኋል ተብለው የተጠሩ እና በሆስፒታሉ በቀዶ ህክምና መኝታ ክፍሎች የሚገኙ 90 ህሙማን ባሰሙት ቅሬታ እረፍት በማይሰጡ ህመም ውስጥ ከመሆናቸው ባሻገር  ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል መጥተው ህክምናውን ለማግኘት  ከወር በላይ ቢጠባበቁም በልብስ ማጠቢያ ማሽን ብልሽት ምክንያት ህክምናውን ማግኘት አለመቻላቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል።

በሆስፒታሉ ሃኪሞች በተለያየ ጊዜያት የተለያዩ ምክንያቶች እየተነገረን ቆይተናል ሲሉ ቅሬታቸውን ያሰሙት ታካሚዎች ችግሩን ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እየተቻለ በልብስ ማጠብያ ማሽን ብልሽት ብቻ ሆስፒታሉ ህክምናውን መስጠት ማቆሙ አሳፋሪ ድርጊት ብለውታል።

ለአንድ  ህመምተኛ የቀዶ ህክምና ለመስጠት እስከ አስር የሚደርሱ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉና ባለሙያዎቹ በቀዶ ህክምና ወቅት ከሚለብሷቸው ልብሶች በተጨማሪ ብዛት ያለው ጨርቅ ይጠቀማሉ።  ቀዶ ህክምና የተደረገበት ጨርቅ ታጥቦ እና ተገቢውን የማድረቂያና ተዋህሲያን ማስወገጃ ክፍል ገብቶ ለሌሎች ቀዶ ህክምና መዘጋጀት ይኖርበታል።

የሆስፒታሉ ሃላፊዎች ለህሙማን የሚሰጠው አገልግሎት እንዳይቋረጥ ተደጋጋሚ ጥረት እንዳደረጉና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ብናሳውቅም ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም ሲሉ ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ ባሉት ሶስት የቀዶ ህክምና ማእከሎች 15 የቀዶ ህክምና ክፍሎች ውስጥ በቀን በአማካኝ ከ 30 እስከ 40 ታካሚዎች ህክምና ይሰጥ እንደነበረና አሁን በሆስፒታሉ በልብስ ማጠብያ ማሽን ብልሽት ምክንያት ታካሚዎች ለበርካታ ጊዜያት ለመቆየት ተገደዋል።