የደብረዘይት ዘር ተኮር ጥቃት ልብ ይሠብራል (መርድ ከተማ)

0

“የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ”

ሰሞነኛው የወላይታ ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው አስከፊ የዘር ጥቃት ይዘገንናል:: ማነሽ ባለተራ ያሠኛል:: አንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ሲገፋ ከማየት በላይ ዘግናኝ ነገር የለም:: የጎሣ ፅዳት (Ethnic Cleansing) ወንጀልም ነው::

የጎሣ ፌደራሊዝም አስከፊ ገፅታውና ጥግ ይህ ነው:: በሃገራችን ውልደትና ቀብር: ፍቅርና ጥላቻ: ሠርግና ፍቺ: እርግማንና ምርቃት፣መቻቻልና የመጣቆስ ጥቃት፣ ፍዘትና ንቃት ፣ ጥፋት ፣ ዕድሳት ሁሉ ጎሣዊ ሆነዋል:: አየሩና ፀሃዩ፣ ጨረቃውና ሠማዩ ጎጠኛና ጎሣዊ ሆኗል:: ሁሉም ነገር ተበክሏል::

የዘር እልቂት የተፈፀመባቸው እንደ ሩዋንዳና አርሜንያ በመሳሰሉት መጀመሪያ ላይ የዘር ጭፍጨፋው ማሟሟቂያው (genocide rehearsal) ይህን ይመስል ነበር:: ለዚህ ነው የጎሣ ፌደራሊዝም አንድም ለጎሣዎች የእርስ በእርስ ግጭት ሌላም ለመገነጣጠል በር ይከፍታል የሚባለው:: የዘር ጭፍጨፋን አስከፊ ውጤትም ለማስረዳት የሁቱ መሪዎችንና ሂትለርን ነቃሽ አርገን ማቅረብ አንችልም:: የጎሣ ግጭት ማህበራዊ መሠረቱ ተሳታፊዎቹ ጎሣዎች ሣይሆኑ የጥፋት ክስተቱን የሚያቀነባብሩ ጥቂት ሃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦችና ለነሱም ክፋትና ግፍ ማበረታቻ ስንቅ የሆናቸው የጎሣ ፌደራሊዝም ርዕዮትና መርዙ ነው::

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋም ይሁን ጎሣ የማንኛውም አካባቢ ባለአደራ እንጂ ባለቤትም አይደለም:: ታዲያ ይህ በቀድሞዋ በርማ በአሁኗ ሚያማር ሂኒንጃ ጎሣ አባላት ላይ እየተካሄደ ካለው የድብቁ የዘር ጭፍጨፋ ግፍ (Myanmar’s Hidden Genocide on Rohingya tribe) በምን ይለያል?