ፋሽስታዊው የሕወሓት አገዛዝ የቆመበትን ኢኮኖሚያዊ ምሰሶዎች ለማሽመድመድ አለም አቀፍ የሃዋላ ተአቅቦ ዘመቻ አካል እንሁን

0

ነአምን ዘለቀ

ከፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ ጋር በሚደርገው ሁለገብ ትግል ስልቶች መካከል የኢኮኖሚያዊ ጦርነት (Economic Warfare) አንዱ ነው። ስርአቱ የቆመበትን ምሰሶ የማዳከም የኢኮኖሚያዊ ጦርነት ስልቶች እንዱ የሃዋላ ተአቅቦ ነው። የሃዋላ ተአቅቦ ለአጠቃላይ ትግሉ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግና ስርአቱን ለማዳከም ያለው ሚና ከፍተኛ ነው።

በፋሽስቱ የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የበላይነት ስር የሚገኘው አምባገነናዊ አገዛዝ በከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ከሶስት ወራት በፊት በስርአቱ ሾልኮ የወጣ የራሱ የብሄራዊ ጸጥታ ም/ቤት የውይይት ሰነድ ያረጋግጣል። ከዚህም በላይ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ፣ እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎች በየጊዜው እንደወጡ ይታወቃል።

ፋሽታዊው የወያኔ አገዛዝ የገባበትን ሁለንተናዊ የፓለቲካና የኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ትተን በውጭ ምንዛሪ በኩል አገዛዙ የደረሰበትን የቀውስ ደረጃ በሚመለከት በቅርቡ በኢሳት፥ ኦሜን፣ ዋዜማ፣ ኣንዲሁም በልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮች የወጡ መረጃዎችን ስንመለከት የቀውሱን ጥልቀት ለመረዳት ይቻላል። ከእነዚህም መረጃዎች ውስጥ የሚከተሉትን ለናሙና እንይ፦
1. የቴሌ፣ የንግድ መርከብ ድርጅት፣ የመብራት ሃይልና ለልዩ ልዩ ፕሮጄክቶች ከውጭ ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል (Debt servicing) በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ መክፈል እንዳልቻሉ፣
2. የአገዛዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ ለሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችን በጀት በገባበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ መሸፈን አለመቻሉ፣
3. በአዲስ አበባ የአርማታ ብረት ዋጋ ሰማይ እየነካ መሆኑ፣ የዶላር ግዢ በጥቁር ገበያ 35 ብር መድረሱ፣ ብረት በ9 ወራት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩ፣ በአዲስ አበባ ብቻ 26 ሺህ የሕንጻ ግንባታዎች ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ ከላይ በተጠቀሱት የሚዲያ አውታሮችና ሌሎችም ተዘግቦአል።
ስርአቱን እየናጡ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ሕዝብ የእምቢተኝነትና የአመጽ ትግሎች ሳቢያ የህወሓት ፋሽታዊ አገዛዝ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ ሌሎችም መገለጫዎችና መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ለዚህም ነው የውጭ ምንዛሪ ተአቅቦ ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ አገዛዙ ከፍጠኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባው። በቅርቡም ወደ ሀገር ውስጥ ግለሰቦች ይዘው የሚገቡትንና ይዘውም የሚወጡትን የውጭ ምንዛሪ ለመቆጣጠርና ለመገደብ አዲስ ህግም እስከማውጣት ድረስ የተገደደው።

ከላይ የቀረቡት መረጃዎች አለም አቀፍ የሀዋላ እቀባ ዘመቻው በስርአቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያመጣ መሆኑን ያረጋግጣሉ። የፋሽስቱ የህዝባዊ ወያኔ ስርአት አገዛዝ አንዱና ትልቁ ጭንቀት የገባበት የኢኮኖሚያዊ ቀውስና ከዚህ ጋር የተያያዘው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቀውስ መሆናቸውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ ነው።

የወያኔ አገዛዝ ከውጭ በሃዋላ የሚያገኘው 4.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የአፈና ስርአቱን ለማንሰራርት፡ ገዳዮቹን፣ አፋኞቹን ለመክፈል፡ ህዝብን የሚጨፈጭፍበት መሳሪያዎች ለመግዛት ጭምር የሚጠቀምበት በመሆኑ፡ የአገዛዙን የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ማድረቅ የትግሉ ትልቅና ወሳኝ አካል መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊና ወቅታዊ ነው።

በኢትዮጵያዊያን አለም አቀፍ ግብረ ሃይል የተጀመረውን የሃዋላ ተአቅቦ ዘመቻ እንደግፍ፣ ለዘመድ አዝማድ፣ ለጓደኞች፣ በማህበራዊ ግንኙነቶችና በሁልም መንገዶች የዘመቻውን አላማና ግብ በማሰራጨት ይህን ዘመቻ ለማጠናከር፣ ግቡንም እንዲመታ ሁላችንም መረባረብ ይገባናል።

ነአምን ዘለቀ