አንዱአለም አራጌና እስክንድር ነጋን ጨምሮ 746 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ መወሰኑን ፋና ዘገበ

አባይ ሚዲያ ዜና
አሰግድ ታመነ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አንዱአለም አራጌ ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።  እነእስክንድርን ጨምሮ ከ700 በላይ የተፈረደባቸውና ክሳቸው በመታየት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ከእስር ይፈታሉ ተብሏል።

ፋና ዛሬ እንደዘገበው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በወሰነው መሰረት በፌደራል ደረጃ በተለይም በሽብር፣ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሀይማኖት አክራሪነት እና በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 417 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታውቋል። ከታራሚዎቹ መካከል 298 በፌደራል ማረሚያ ቤት፣ 119ኙ ደግሞ በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ናቸውም ተብሏል።

ታራሚዎቹ የሚፈቱት ዝርዝሩ ለሀገሪቱ ርእሰ ብሔር ቀርቦ ሲፀድቅና የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ዜናው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ያስደሰተ መሆኑ እየተነገረ ነው ።

በተያያዘ ዜና በሃሰተኛ የሽብር ክስ ተከሳ የ4 ዓመት ከ5 ወር እስራት የተፈረደባት የሰማያዊ ፓርቲ አባልል፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍርዷን ጨርሳ ዛሬ መፈታትዋ ተነግሯል።

የተገኘውን ድል በመቀበል፣ በተገኘችው ትንሿ ድል ሳንዘናጋ፣ ህዝቡ ለበለጠ ነጻነትና ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚያካሂደውን ተጋድሎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተነግሯል።

27655111_1961396847222638_6777536547305978998_n