የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ከመፍታቱ ጎን ለጎን የፍትህ ስርዓቱ አስተማማኝ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ መንግስት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን  ለመፍታት መወሰኑ አስደሳች ዜና መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ መንግስት ከ700 በላይ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን  ለመፍታት መወሰኑ መልካም ጅምር ቢሆንም ተፈችዎቹ በቀጣይ ስራቸውን እንዲያከናውኑ እና የሃሰት ክስ ተመስርቶባቸው በድጋሚ እንዳይታሰሩ ዋስትና የሚሰጡ እርምጃዎች መኖር አለባቸው ብሏል። እስረኞቹን ከመፍታት ጎን ለጎን የፍትህ ስርዓቱ አስተማማኝ ሊሆን እንደሚገባም ገልጿል።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶችም ውሳኔውን በማወደስ መግለጫ አውጥተው ሁሉም የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ እያደረጉ ያለውን ግፊት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

የህሊና እስረኞቹ ስራቸውን ስለሰሩ ብቻ ቀድሞም መታሰር እንደማይገባቸውና ከእንግዲህ አንዲት ቀን እንኳን በእስር ላይ መቆየት የለባቸውም ብሏል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ መንግስት ከ700 በላይ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን  ለመፍታት መወሰኑን ለአገዛዙ ቅርበት ያለው መገናኛ ብዙሃን ከገለፀ በኋላ በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጪ የሚኖሩ እትዮጵያውያን በተለያዩ ድህረ ገፆች ደስታቸውን በመግለፅ መወያያ ርዕስ መሆኑ ቀጥሏል።