በመንግስት ታጣቂዎች እና በአርበኞች ግንቦት ሰባት መካከል ግጭት እንደተከፈተ ተሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም

በሰሜን ጎንደር ጭልጋ ሎዛ ወረዳ ድብላ ቀበሌ የመንግስት ታጣቂዎች እና የአርበኞች ግንቦት 7 ሃይሎች ተኩስ ሲለዋወጡ እንደነበረ ተገለጸ። ግጭቱ የተቀሰቀሰው የካቲት 2 ቀን 2010 ዓም እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

ግጭቱ በአከባቢው የሚኖሩ ገበሬዎች የተጣለባቸውን ከአቅም በላይ የሆነ ግብር ለመክፈል ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ አመጽ ሲቀሰቅሱ ነበሩ የተባሉትን ገበሬዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ ጥረት እንደሆነ ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ገበሬውን በማነሳሳት አመጽ ለመቀስቀስ ሲጥሩ ነበሩ የተባሉትን ሰዎች ለማፈስ ወደ ቦታው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመንግስት ወታደሮች ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደሮች ድንገተኛ ጥቃት እንደተከፈተባቸው ተነግሯል። 

በጥቃቱም ከመንግስት ወገን ሁለት ወታደሮች ህይወታቸው እንዳለፈ ሲገለጽ አንድ ወታደር ክፉኛ እንደቆሰለ ተነግሯል። የደፈጣ ጥቃቱን ከሰነዘሩት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ወገን ስለ ደረሰ ጉዳት  ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰአት ድረስ አልተገለጸም።