እነ እስክንድር ነጋና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ እንዲፈርሙ ተጠየቁ

0

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

የኢትዮጵያ መንግስት በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ ይለቀቃሉ ካላቸው ከ700 በላይ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች መካከል እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ እና ክንፈሚካኤል ደበበ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የግንቦት 7 ንቅናቄ አባል ነበርኩ ብለው እንዲፈርሙ በድጋሚ መጠየቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ገለጹ።

በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ እንዲፈርሙ መጠየቃቸውም ታውቋል።

ከ20 ዓመት በላይ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት አህመዲን ጀበል፣  አህመድ ሙስጠፋ፣  ካሊድ ኢብራሂም እና መሃመድ አባተ “በጥፋታችን መሰረት ተፈርዶብን እስር ላይ ስላለን ተፀፅተን ጥፋታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀን ፈርመናል” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ለእያንዳንዳቸው እንደተሰጣቸውና “ያጠፋነው ነገር የለም” በማለት ሳይፈርሙ መቅረታቸውን ቤተሰቦቻቸው አሳውቀዋል።

በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙ 55 ሰዎች የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ እንዲፈርሙ በማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች እንደቀረበላቸው መስማታቸውን የሙስሊም አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ቤተሰቦች ተናግረዋል።

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው ሲፒጄ፣ የፀሃፊያን ማህበር የሆነው ፔን ኢንተርናሽናል፣ የአሜሪካው ሴናተር  ማርኮ ሩቢዮ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር የኢትዮጵያ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስረኞችን እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።