የጀግና ልጅ እናት ታጥቃለች በገመድ! (ከድንበሩ ደግነቱ)

0

የክንፈ ሚካዔል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እናት፥ ብፅዓት ወልደ ጊዮርጊሥ ልጃቸው ለወገኑ መብት በቆመ በወስላቶች ከተወሰደባቸው ሥድስት ዓመት ከሥድሥት ወር ሆነው። ይሄን ሁሉ ዘመን በፀሀይ፥ በዝናብ፥ በጭቃ፥ በትራንስፖርት ወረፋ፥ በባለጌ የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎችና አስተዳዳሪዎች ግልምጫ፥ ስንቱን ችለው ስንቅ ሲያቀብሉ ኖሩ። በፍትህ የሚያላግጡትን ዳኛና ዓቃቤ ህግ ጭካኔና የማታውን የኢቲቪ ውሽት እስኪያንገሸግሻቸው ነው ይህን ሁሉ ዘመናት የተጋቱት። በነፃ የውጪ አገር ዜና ማሰራጫዎች እየቀረቡ የህግ ትንታኔ የሚሰጡትን ጭፍን በልቶ አይጠግቤ ዘረኛ ምሁራንን ቅጥፈት ጆሮዋቸው እስኪደማ ድረስ አድምጠዋል። አቤት እንዴት ቻሉት ይሆን!

ከጠንካራ መንፈሥና ሙሉ ዐካሉ ጋር የወሰዱትን ልጅ የመስማት ብቃቱን ቀንሰው ሊመልሱላቸው ቃል የገቡት እነ መሀላ ፉቲዎች፥ ቃላቸውን አጠፉ። ይህን ሁሉ መከራ የቻሉት ጀግና የጀግና እናት አንድ ነገር ብቻ ከበዳቸው። ለአገራቸውና ለባንዲራቸው በከፈሉት መስዋዕትነት በመኩራት ፈንታ ይቅርታ መጠየቅ። ባንዲራና የአገር ፍቅር በሌላቸው ዕኩዮች ለደረሠባቸው በደል ይቅርታ በመጠየቅ ፋንታ ልጃቸው ይቅርታ ጠይቆ እንዲፈታ ማድረግ። ህወሀት ብልግናና ጭካኔውን ባባሰ ቁጥር ይኸው እንስፍስፉ የእናት አንጀት ሳይቀር በአገር ፍቅር ስሜት እየደነደነ ለኢትዮጵያ ነፃነትና ለዜጎችዋ ክብር ልጅዋን ከመገበር ወደሁዋላ ላለማለት ጨክኖዋል። ዕምዬ “ልጄ ለዓላማው ነው ቢሞትም አላዝንም አለች።”  https://www.youtube.com/watch?v=mn4TfG9nmR4

“በጣም የማዝነው በ2010 የካቲት 1 ቀን እፈታለሁ ብሎ ለዓለም እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተናገረው ቃል ሕዝብም ሆነ እኛ ደስ ብሎን ነበር። በሁለት እንደገና እነሱን ተጠያቂ አድርጎ ፈርሙ ማለት በእውነት ነው የምላችሁ ለእኔ ለግለሰብዋ እንኩዋን ያሳፍረኛል። በጣም ነው የሚያሳፍረው። ኢትዮጵያን የሚያክል አገር የሚገዛ እንደገና ግንቦት ሠባት ነኝ በሉ! ለታሣሪው ቤተሰብም ሆነ ማረሚያ ቤት ላሉት በጣም ነው የማዝነው። አንፈርምም ላሉት በጣም ተደሥቻለሁ። ….ለዓላማው ገብቶበታል። ቢሞት ልጄ አላዝንም። እውነትን ይዞ ነው። ለሀገር ትግል ከአያት ቅድመ አያት የመጣ ነው። አዲስ ነገር አይደለም። የማዝነው ለሊቱን ተጠንስሶ ተጠምቆ በአንድ የተናገሩትን በሁለት አንደገና መሣታቸው ያሳዝናል።”

ማነህ በቀደም ለት ቪኦኤ ላይ  ቀርበህ “ሌላውን አልሰማሁም የሰማሁት የአቶ ንጉሡ ጥላሁንን ንግግር ብቻ ነው” ብለህ ቀጥፈህ ህወሀትን ለማዳን የሞከርክ ምሁር፥ ይልቅ እኚህን እናት አድምጥና ህወሀትን ምከር። ከሕግ ትቤት ስትመረቅ የገባኸውን መሃላ ወደጎን ገሸሽ አርገህ ወይ ለሆድህ ወይ በዘረኝነት ልክፍት ዋሽተህ እንቅልፍ ወስዶህ አደረ። ይህች እናት ልጄ ተገዶ በውሽት ከሚፈርም አንገቱ ላይ የገባው ሸምቀቆ ይጥበቅበት እያለች ነው። እርግጥ ሰሞኑን የምታዩት ወታደራዊ ሠልፍ የማይደፈር ግንብ ሊመስል ይችላል። ግን ከኚህ እናት መንፈሥ አይጠነክርም። የኢትዮጵያን ሕዝብ ገላችሁ አትጨርሱም። ብትጨርሱም ወላድ በድባብ ትሂድ ጀግና ተወልዶ ይተካል። ሰከን ብሎ ማሰቡ ግን ለሁሉም ይበጃል። መማር ለመቼ ነው?