ጀርመን የሚገኘው የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት የኢትዮጵያና የጀርመን መንግስታት ያደረጉት የስልክ ውይይት ላይ ትችት አቀረበ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያደረጉት የስልክ ውይይት ትችት እየቀረበበት ነው።

ጀርመን የሚገኘው ለተጨቆኑ ህዝቦች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት (Gesellschaft für bedrohte völker)  ሃላፊ ኡልሪሽ ዲሊዮስ የጀርመን መንግስት ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሁለት አመታት ድጋፍ በሚፈልጉበት ወቅት እንዳልደረሰላቸው አሳውቀዋል። ኢትዮጵያውያን በአስጨናቂ ሁኔታ ላይ ወድቀው በነበረበት ወቅት ሜርክልና መንግስታቸው  የት ሆነው ነው አሁን ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር የስልክ ውይይት ያደረጉት በማለት እኚሁ የመብት ተከራካሪ ትችታቸውን ገልጸዋል።

አገዛዙን በይፋ በተቃወሙ ኢትዮጵያውያን ላይ ላለፉት ሁለት አመታት ሲፈራረቅ የነበረውን ስቃይና ጭቆና ለማስቆም የጀርመን መንግስት ያደረገው አንዳች ነገር የለም በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እና መርሃ መንግስት አንጌላ ሜርክል ያደረጉትን የስልክ ውይይትን አልሪሽ ዲሊዮስ ተችተዋል።

የጀርመን ልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸውን የገለጹት የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት ሃላፊው በምን ርዕስ ላይ  እንደሚወያዩ ግን በግልፅ የታወቀ ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የገባበት አጣብቂኝን በመመርኮዝ በጀርመን እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓ አገራት ጥገኝነት ጠይቀው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው በግዳጅ እንዲመለሱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እነዚሁ የጀርመን ልኡካን ቡድንኖች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሊወያዩ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ኡልሪሽ ዲሊዮስ በተጨማሪ አሳውቀዋል።

ጀርመን የኢትዮጵያ የልማት ተባባሪ ሃገር እንደሆነች በመግለፅ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት ልኡካን ቡድኑ ትኩረት ሰጥቶ የሚወያየው በኢትዮጵያ ንፁሃን ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መገደል አሊያም በየቀኑ እየከፋ ስለመጣው የመብት ረገጣ ሳይሆን በአውሮፓ በሚገኙ ስደተኞች ጉዳይ ላይ እንደሆነ በመተቸት ኡልሪሽ ዲሊዮስ  ተናግረዋል።

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገዛዙ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመንግስት ወታደሮች እየፈጸሙ ያለውን ግድያ እንዲሁም የመብት ጥሰት ለአለም ለማጋለጥ እና ለመቃወም የፊታችን የካቲት 15 ቀን 2010 ዓም (22 Feb. 2018 እኤአ) የተቃውሞ ሰልፍ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ለማድረግ መርሃ ግብር እንደያዙ ተገልጿል።