“ልጄ ናፍቆኛል አሁኑኑ ደውዬ ባለቤቴን እና ልጄን አነጋግራቸዋለሁ” ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤኔዘር አህመድ

መንግስት የህሊናና የፖለቲካ  እስረኞችን ለመፍታት በገባው ቃል መሰረት በዛሬው እለት እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ ከ700 በላይ እስረኞች ከእስር ለቋል።

ከእስር ከተለቀቁት መካከል የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ  አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ካሊድ ኢብራሂም እና መሃመድ አባተ፣ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር  አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ወሮ እማዋይሽ አለሙ እንዲሁም አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ይገኙበታል።

በትላንትናው እለት  ከእስር የተለቀቁትና ዛሬ በአዳማ ከተማ ከፍተኛ የህዝብ አቀባበል የተደረገላቸው አቶ በቀለ ገርባ ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  በፌደራል ማረሚያ ቤቶች በርካታ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች እንደሚገኙ ገልፀው፣ አሁን እየተፈቱ ካለው ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ አሳውቀዋል።

አቶ አንዱዓለም አራጌ ከእስር ከወጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም እንደሚኮሩና እንደሚመኩ ገልፀው፣ የህዝቡ አቀባበል ከጠበቁት በላይ  እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።

ለሁላችንም መንጋት አለበት የማይጠፋ የዲሞክራሲ ፀሃይ በኢትዮጵያ ምድር ወጥቶ ሁላችንም የምንኮራባት፣ ለአንዱ ጨለማ ለሌላው ብርሃን የማይሆንባት፣ የሚጠበቀው ንጋት ለሁሉም የሚበራበትን ጊዜ ለመላ ኢትዮጵያውያን እንደሚመኙ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከሰባት አመታት በላይ የታሰሩት ፖለቲከኛው አቶ አንዱአለም አራጌ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለአመታት በእስር ላይ ቢያቆያቸውም አለም አቀፍ ሽልማትን በተደጋጋሚ ማግኘት የቻሉት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠየቅ ልጃቸው እንደናፈቃቸውና በስልክ የልጃቸውን እና የባለቤታቸውን ድምፅ ለመስማት እንደጓጉ ተናግረዋል።

የህዝቡ የዲሞክራሲ ጥያቄ ጎልብቶ አምባገነኑን ኢህአዲግን እንዳንገዳገደው የተናገሩት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሰላማዊ ትግሉ የሚቀጥልበትን መንገድ እያሰቡ እንደሆነ ገልፀዋል። አለም አቀፍ ሽልማቶችን ያገኙት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በአንድ በኩል ተስፋን በሌላ በኩል አደጋ በመያዝ መንታ መንገድ ላይ እንደሚገኝ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አሁን በአገሪቱ የሚታየው ትግል እዚህ እንዲደርስ ብዙ ሰዎች መሰቃየታቸውን፣ መታረዛቸውን፣ መራባቸውን፣ መሰደዳቸውን፣ መታሰራቸውን እንዲሁም ህይወታቸውንም መስጠታቸውን ለጋዜጠኞች በሰጡት ንግግራቸው አስታውሰዋል። ለነፃነት የታገሉት እነዚህ ሰዎች ይህን  ሁሉ ስቃይ የተቀበሉት ተስፋን ሰንቀው እንጂ ኢህአዴግ ላይ ጥላቻንና ቂምን ሰንቀው እንዳልሆነም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ገልጸዋል።

በብሄር ላይ ያተኮረ ጥቃትን እንዲሁም በፋብሪካዎች ላይ የሚደረግ ቃጠሎን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ኮንነው ስልቱን አበላሽተን ግቡን ማሳመር አንችልም በማለት የብሄር ጥቃቶችና የፋብሪካ ቃጠሎዎች ለትግል ያነሳሳንን ተስፋ የሚያጨልሙ ተግባሮች እንደሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል። እንደ እነዚህ አይነት ድርጊቶች ዛሬ ነገ ሳይባል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ መቆም እንዳለባቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ኢህአዴግ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከተቃዋሚ አካላት ጋር መወያየት እንዳለበትም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አሳስበዋል።

በእስር ቤቶች ውስጥ በርካታ የኦሮሞ ልጆች እንዲሁም ከጎንደርና ከተለያዩ የአማራ ክፍሎች የታፈሱ ቁጥራቸው ብዙ የሆኑ ግለሰቦች እንደሚገኙ ከእስር ነፃ የወጡት በይፋ እየመሰከሩ ይገኛሉ። በእስር ቤቶች በሚገኙ የማሰቃያ እና የጨለማ ቤቶች ውስጥም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የግፍን ፅዋ እየተጎነጩ ያሉ ሰዎች እንደሚገኙ በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ነፃ የተለቀቁት ግለሰቦች በመግለፅ፤ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች መንግስት ነፃ እንዲለቅ  የሚደረገው ግፊት መቀጠል እንዳበት ጠቁመዋል።

ከእስር በነፃ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመቀላቀል በበቁት ውድ ኢትዮጵያኖች ደስታችንን በመግለፅ የተቀሩት የፖለቲካ፣ የህሊና እስረኞች እና ጋዜጠኞች ነፃ ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የአባይ ሚዲያ አባላት ምኞታችንን እንገልፃለን።