የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ለቀቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
ግርማ ቢረጋ

በጠቅላላው የሃገሪቱ ከተሞች በተለያየ ግዜ ይደረግ የነበረው መንግሥትን የማቃወም እንቅስቃሴ ከመቼውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉ መንግሥት ሳይወድ በግዱ አሁን ወደተያያዘው እሥረኞችን የመፍታት ሂደት እንዲገባ አድርጎታል።

ትናንት ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር ከተፈቱት ስድስት ግለሰቦች በተጨማሪ ዛሬ ደግሞ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ የአንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) አመራር የነበረው አቶ አንዱአለም አራጌ፣ አቶ አህመዲን ጀበል፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ኡስታዝ መሐመድ አባተ፣ ኻሊድ ኢብራሂም፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) እና በአርበኞች ግንቦት 7 ስም የታሰረው አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ የአኝዋክ ተወላጆቹ ኦኬሎ አኳይ፣ ጋሌ ደንግ፣ ኦጂር ኦተው፣ ኦጁሉ ዌሎ፣ ኦዊር፣ እና አዳዩ ኦኬሎ ተጠቅሰዋል።

እንደሁም በዛሬው እለት ከተለቀቁት መካከል በነጀነራል ተፈራ ማሞ መዝገብ ተከሳ ለረዥም ጊዜ በእስር ቤት ስትማቅቅ የነበረችው ወ/ሮ እማዋይሽ ለረዥም ጊዜ የታሰሩት የኦሮሞ ፖለቲከኛ ኦልባና ሌሊሳ ተፈተዋል።

በዚህም ሂደት ላይ ህዝቡ በነቂስ በመውጣት ጀግኖቻችን እያለ በመቀበል ደስታውን በጭፈራ እና በእልልታ አጅቧቸው ረጅም መንገድ በመጓዝ ሲገልጽ ተስተውሏል ።

በትላንትናው እለት ከእስር የተለቀቁት አቶ በቀለ ገርባ ”ምንም እንኳን እኔ ከእስር ብፈታም በርካቶች ለዴሞክራሲ፣ ለእኩልነት፣ ለብልጽግናና ለአገር አንድነት ዋጋ በመክፈል ሲጽፉ፣ ሲናገሩና ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች አሁንም ድረስ እስር ቤት ናቸው፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ ደስታዬ የተሟላ እንዳይሆን ያደርገዋል፣ ብለው እንደነበረ አይዘነጋም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከእስር የተፈታው እስክንድር ነጋ በተደጋጋሚ የጀመርነውን ሰላማዊ ትግል እንቀጥላለን በማለት ድምፁን ሲያሰማ ተስተውሏል ።