ወልቂጤ በታላቅ የህዝባዊ ትግል እየተናጠች ነው

አባይ ሚዲያ ዜና
አሰግድ ታመነ

በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች የተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ አድማሱን በማስፋት ወደ ወልቂጤ ተዛምቶ በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች  የእሳት ቃጠሎ ደርሷል።

ትላንት ተጀምሮ የነበረው የስራ ማቆም አድማ  ዛሬም በመቀጠል ወደ አደባባይ ተቃውሞ ተቀይሯል። በርካታ ህዝብ የተሳተፈበት ሲሆን ከተማው በጪስ ተሞልቷል። የገቢዎች ቢሮ መውደሙ እና የመንግስት መኪኖች መቃጠላቸውም እየተነገረ ነው።

በወልቂጤ ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ህዝቡ ቀጥታ መተኮሳቸው የተነገረ ሲሆን በዚህም በርካታ ሰዎች መገደላቸውና መቁሰላቸው ተገልጿል።

ከትላንት ጀምሮ ምንም አይነት አገልግሎት በከተማው የተቋረጠ ሲሆን በዛሬው እለት መንገዶች ተዘግተዋል ከተማዋ በተኩስ እና በጭስ የጦር አውድማ መስላለች። አመፁ ወደሌሎችም የጉራጌ  ዞኖች ይስፋፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ወልቂጤ ውስጥ በተነሳው ህዝባዊ እንቢተኝነት የሟቾች ቁጥር 10 ደርሷል። ህዝባዊ እንቢተኝነቱ ወደ ጉብሬና (ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ወደሚገኝበት) እምድብር (ቸሃ ወረዳ) ተዛምቷል ተብሏል።