ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚንስትርነታቸው በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቁ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ድርጅታቸው የጀመረው የመታደስ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆንና ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር ያስቀመጣቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ በፈቃዳቸው የፓርቲያቸውንና የኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸውን እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትርነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም በሰጡት መግለጫ፣ ያቀረቡትን የመልቀቂያ ጥያቄ የድርጅታቸው ደህዴንና የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የተቀበላቸው መሆኑን ተናግረው፣ ያቀረቡት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው በኢህአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ በሚያደርገው ስብሰባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ውሳኔ የደረሱበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ የሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ህዝብ ለሚያቀርባቸው በርካታ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው ከሚል በራሴ ፈቃድ ያቀረብኩት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ 

ያቀረቡት የስልጣን መልቀቂያ ውሳኔ አግኝቶና የተወካዮች ምክር ቤት ተተኪውን ጠቅላይ ሚንስትር እስኪመርጥ በስራቸው ላይ እንደሚቆዩም ተናግረዋል፡፡