ለምን ዝናብ ይጣል! (ከይመር ቦሩ )

0

02/12/2018)

ከአምቦ እስከ ጎንደር

ከመቱ ባሕር ዳር

ከጨለንቆ መርሳ

ኮፈሌና አሳሳ

ከጅማ አዋሳ

ሃራ ሀመሬሳ

ከሰማራ ዲላ

ከደጋን ጋምቤላ

ሃርቡን መለስ ገርባ

ቆቦ አዲስ አበባ

ጉራ ፈርዳን ጠቅሶ

ከወልዲያ ኮንሶ

ከዳር እስከዳር

በኢትዮጵያ ምድር

በዓልሞ ተኳሽ፣ ግንባር ግንባሩን

በፌደራል ዱላ፣ መሃል አናቱን

መላ አካላቱ፣ባግዓዚ ጥይት

ያልተነዳደለ፣ ልክ እንደወንፊት፤

እግሬ አውጪኝ ሲሮጥ፣ ከኋላ ተመትቶ

ቀን የጨለመበት፣ ባፍጢሙ ተደፍቶ

ያልቀረለት ጭራሽ፣ ጥይትና ዱላ

ነፍሱ ከከዳችው፣ ከሞተም በኋላ

ፍጹም ስለለ፣ ሲቀር አንድ ክልል

ኧረ አትጸልዩ ለምን ዝናብ ይጣል?

በወገናችን ደም፣ መሬቱኮ ጠግቧል!

*            *             *

በመትመም ላይ ባሉ፣ አጅበው ታቦት

ምእመናን፣ ወንድ ሴት፣ ወጣት አዛውንት፤

ፍፁም ሳይጠበቅ፣ ምንም ሳይታሰብ

አግዓዚ ተስቦ፣ በልቡ እንደእባብ

በከፈተው ተኩስ፣ ምንም ሳያቅማማ

ጥምቀቱን አረገው፣ የሬሳ አውድማ።

ክረምትን መጠበቅ፣ መቸስ ቢያስፈልግ

እስኪበቃው ጠግቦ፣ መሬቱ በበልግ።

መርሳ ቆቦን ይዞ፣ ሃራና ወልዲያ

ከንግዲህ መሬቱ፣ አይሻም ማዳበሪያ!

ኧረ አትጸልዩ ለምን ዝናብ ይጣል?

በወገናችን ደም፣ መሬቱኮ ጠግቧል!

*           *           *

ፆማቸው አብቅቶ፣ በገባ በወሩ

በአካባቢያቸው፣ ኢድን በሚያከብሩ

ከዳር እስከዳር፣ ቁጭ ብለው በተርታ

በሚያስተጋቡት ላይ፣ ምስጋና ለጌታ

በኮፈሌ አሳሳ፣ በንፁህ ሰማይ ስር

በዋናው መሥጂድም፣ በታላቁ አንዋር

ከነጫማውና፣ ከነጭቃው ገብቶ

አግዓዚ ፌደራል፣ በጭፍን ተኩስ ከፍቶ

እንኳን ፈታላችሁ፣ ፆመልጓሙን

ያለው በማጨድ ነው፣ የሚበቃውን።

ኧረ አትጸልዩ፣ ለምን ዝናብ ይጣል?

በወገናችን ደም፣ መሬቱኮ እርሷል!

*            *           *

አጊጠው ተውበው፣ በወግ በየመልኩ

አሮጌውን ዘመን፣ ባዲሱ ሊተኩ

ከሁሉም አቅጣጫ፣ ከኦሮሚያ ክልል

ለማክበር በመጡ፣ የኢረቻን በዓል፣

ቢሾፍቱ ሜዳውን፣ ባደረጉት ጢም

አግዓዚ ቶክስ ከፍቶ፣ ባፈሰሰው ደም

የውድ ሃገራችን፣ መሬቷኮ እርሷል

ኧረ አትፀልዩ፣ ለምን ዝናብ ይጣል?

*          *         *

ያገሬ ገበሬ፣ ቦይ መቅደድ አቁም

ውሃው ስላለበት፣ የወገንህ ደም።

አትቅዱ ቦርከና

ብቅ አትበሉ ጣና

ወደአባይ አታቅኑ፣ አዋሽ አትውረዱ

ዋቢም ይቅርባችሁ፣ ኦሞም አትሂዱ

ሆራም አያዋጣ፣ እንዲሁም ቢሾፍቱ

ተከዜማ ጭራሽ፣ ብቅ ማለት ከንቱ፤

ሃይቅም ሆነ ወንዙ፣ ተለቀም አነሰ

በወገናችን ደም፣ ስለደፈረሰ።

ወይም አይናችሁን፣ ሸፍኑ በጃችሁ

አማራጭ ከጠፋ፣ መቅዳት ካለባችሁ።

ድርቅ ገባ አትበሉ፣ ዝናቡ ዘገየ

እያያችሁ መሬት፣ በደም የጨቀየ፤

በወላጆች እምባ፣ በየቲሞች ለቅሶ

እያያችሁት፣ አገር ምድር እርሶ።

ዝናብ ልጣልስ ቢል፣ ከምን ላይ ሊከርም

ተይዞበት ቦታው፣ በንጹሃን ደም።

ኧረ አትጸልዩ ለምን ዝናብ ይጣል?

በወገናችን ደም፣ መሬቱኮ ጠግቧል!

*             *             *