ኦህዴድ (OPDO) ከኢህአዴግ ወጣ ባለ መንገድ በህገመንግስታዊነት (Constitutionalism) መንገድ ጉዞ ጀመረ እንዴ (ከፍትህ ይንገስ )

ህገመንግስታዊነት (Constitutionalism) ሲባል የመግስት ስልጣን የሚገኘው ከህዝብ መሆኑን አምኖ መቀበልና ይህንን ስልጣንም በህገመንግስት የመገደብ አሰራር መፍጠር ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በአንድ ሃገር ዉስጥ የሚገኝ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ ህገ መንግስት በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር  ማድረግ የሚገባዉንና የማይገባዉን ድርጊት ግልጽ በሆነ መንገድ ያስቀመጠ መሆን አለበት ማለት ነው።  በርግጥ ባንድ ሃገር ዉስጥ ሀገመንግስታዊነት አለ ለማለት የህገመንግስት መኖር ብቻዉን በቂ አይደለም ፤ ምክንያቱም ማንም አምባገነን የሆነ መንግስት ህግመንግስት መጻፍ ይችላልና ነው።

ይልቁንም ህገመንግስታዊነት አለ ሊያስብሉ ከሚችሉ ሁኔታወች መካከል በህገመንግስቱ የሰፈሩ በአለም አቀፍ  ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ተቋማት እንዲገነቡ ማድረግ፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲአዊ መብቶች እንዲከበሩ ማስቻል፤ እኩልነት እና እኩል ተጠቃሚነትን ማስፈን እናም ሌሎች መሰል መብቶችን ማስከበርን ያካትታሉ። በሌላ አነጋጋ;ር ህግመንግስታዊነት ሲባል ህገመንግስቱ ሳይሸራረፍና ሳይጓደል መፈጸምንና ማስፈጸምን ይመለከታል ። ከዚህ አንጻር  የብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ህወሃትና ደኢህዴን ስብስብ የሆነው ኢህአዴግ በምን መልክ ይገለጻል  የሚለዉን ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ሁሉም እንደሚያቀው ኢህአዴግ እንዲጸድቅ ያስደረገው ህገመንግስት አለ። ይህ ህገመንግት ችግሮች ሊኖሩበት ቢችሉም ዘመናዊ የሆነና ተግባር ላይ እየዋለ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አጣብቂኝ ዉስጥ አትገባም ነበር። ችግሩ ያለው ህገመንግስቱ በዋንኛነት በኢህአዴግ በራሱ እየተሸራረፈ ብቻ ሳይሆን እየተጨፈለቀና  እየተረጋገጠ መሆኑ ላይ ነው። ይህ ማለት ምን  እንደሚመስል በሚከተሉት ማሳያዎች ግልጽ ማድረግ ይቻላል።

የመጀመሪያዉና ትልቁ ችግር ያለው  በህግመንግስቱ የተቀመጠዉን የብሄር ብሄረሰቦች  እና ህዝቦች የእኩልነት መብት መርህ በራሱ በኢህአዴግና በሚመራው መንግስት እተጨፈለቀ ያለ መሆኑ ላይ ነው። በህገመንግስቱ የነዚህ ብሄር ብሄረሰቦች መብቶች እውቅና የተሰጣቸው ቢሆንም ባፈጻጸም ረገድ ግን ከሁሉም በላይ እኩል የሆኑት ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የህወሃት አባላት፣ ደጋፊወቻቸዉና በዙሪያቸው  ያሉ ሰወች ብቻ ናቸው። ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የፖለቲካዉንም ይሁን የኢኮኖሚውን እንዲሁም የማህበራዊ ድባቡን የተቆጣጠሩት  እነዚሁ የህወሃት ሰዎች ናቸው። ለስሙ ሁሉም ብሄር እና ብሄረሰቦች ራሳቸዉን በራሳቸው እያስተዳደሩ እንደሆነ  ቢገለጽም እየተመሩ ያሉት ግን የህወሃት ሰዎች ከፍተኛዉን ተጽእኖ  በሚያሳድሩበት ኢህአዴግ ዉስጥ በሚፈልቁ ፖሊሲዎች፣ ህጎችና መመሪያዎች መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። ለዚህም ሲባል ዴሞክራሲአዊ ማእከላዊነት እንደዋነኛ መሳሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል  ። በዚህ ረገድ የድንበር ማካለሉን እንደአንድ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ይህን በተመለከተ ይኖሩባቸው የነበሩ ህዝቦችን ሳያስወስን ያለምንም ጥያቄ ህወሃት ወደራሱ ያጠቃለላቸዉን ለም የሆኑ የሁመራና የወልቃይት አከባቢወችን ማየት ብቻ በቂ ነው።

በማሳያነት ማንሳት የሚቻለው ሁለተኛው ጉዳይ ኢህአዴግ ህገመንግስታዊ እውቅና በተሰጣቸው የተቋማት ግናባታ ላይ የጸና  እምነት የሌለው መሆኑ ነው። በርግጥ የተፈጠሩ ተቋማት የሉም ማለት አይቻልም። ይሁንና እነዚህ ተቋማት ገለልተኛ ፣ ነጻና ጠንካራ እንዲሆኑ አልተፈለጉም።  የተፈለጉት በኢህአዴግ ሳንባ ብቻ እንዲተነፍሱና የሱ ፍላጎት ማስፈጸሚያ እንዲሆኑ ነው። እንደዉም አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ብቻ ሳይሆኑ እንደተቋማቱም ይቆጠሩ እንደነበረ መካድ አይቻልም። እርሳቸው በሂወት በነበሩበት ጊዜ ይገነቡ የነበረው የራሳቸዉን ተክለ ሰዉነት (Personality Cult) እንጅ ተቋማቱን አልነበረም። ይህም በመሆኑ የእርሳቸው ህይወት ካለፈ በኋላ በተፈጠረው የአመራር ክፍተት (leadership Gap) ሳቢያ  ኢህአዴግ እረኛው እነደጠፋበት በግ በመዋተት እና በመደናበር ላይ ይገኛል። ከርሳቸው ስብእና ይልቅ የተቋማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሆን ኖሮ በኢህአዴግ ዉስጥ አሁን የተፈጠረው መደናበርና የቅቤ ገበያ የሚመስል አካሄድ  አይከሰትም ነበር።

አሁን በተጨባጭ ያሉት የተቋማት ሁኔታ በሚታይበት ጊዜ ከፍትህ ተቋሙ እስከምርጫ ቦርድ፤ ከጸጥታ ተቋማቱ እስከ ሰብአዊ መብት እንዲሁም እንባ ጠባቂ ተቋማቱ የኢህአዴግና የኢህአዴግ አላማ ማራመጃ እንደሆኑ መካድ አይቻልም።ከነዚህ ዉስጥ ደግሞ በተለየ መንገድ የጸጥታ ተቋማቱ ላይ ብናተኩር ከኢህአዴግ ገለልተኛ አለመሆናቸውን ትተን ከዚህ ይባስ ብሎ በህወሃት ሰዎች የሚሽከረከሩና የሚዘወሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህ በመሆኑ ደግሞ የህወሃት ሰዎችን ትምክህት እንዲወጥራቸውና ከኛ በላይ ላሳር ነው እንዲሉ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያን ህዝብ በጸጥታ ሃይሉ ብቻ አፍነን እንገዛለን የሚል ቀቢጸ ተስፋ ዉስጥ የገቡት። በህወሃት ሰዎች ዉስጥ የዚህ አይነት አስተሳሰብ በስፋት እንዳለ የሚገለጽበት አንዱና ዋነኛው መንገድ በተለያየ ጊዜ አንጃና ቡድነኝነት የሚፈጠርበት  ስብስብ መሆኑ ነው። በ1993 ዓ.ም ህወሃት ዉስጥ አንጃ ተፈጥሮ ሌሎቹን ድርጅቶች ሲያተራምስ የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። የህወሃቱ አንጃ ከሰራዊቱ፣ ከደቡብ ህዝቦችና ከኦህዴድ ቁልፍ የሆኑ ሰወችን በመያዝ ብአዴን ዉስጥም ባይሳካለትም ሙከራ በማድረግ ስልጣን ሊቆጣጠር ሞከረ። አሁን ባለንበት ወቅት  ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ ህወሃት ዉስጥ የተፈጠረው  ቡድነኝነት ኦህዴድ እና ሌሎች ድርጅቶች  ዉስጥም ለመግባት ሞክሮ እንደነበር ኢህአዴግ አደረኩት ባለው 17 ቀናት በወሰደው ግምገማው  ለየኋቸው  ካላቸው ችግሮች አንዱ ሆኖ በተለይ በአቶ ለማ መገርሳ በኩል በግልጽ ቀርቧል። ትልቁ ነገር ያለው  አንጃው መፈጠሩ ላይ አይደለም፡  ቁምነገሩ ያለው  ለምንድን ነው ብዙዉን ጊዜ አንጀኝነትና ቡድነኝነት  ህወሃት ዉስጥ የሚፈጠረው የሚለው ላይ ነው። አንጀኝነትና ቡድነኝነት ህወሃት ዉስጥ የሚፈጠረው ሃገርን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የጸጥታ ተቋማት ማለትም መከላከያ ሰራዊቱ፣ ደህንነቱና ፖሊሱ ዞር ዞሮ በህወሃት  ሰውች ቁጥጥር ሲር የወደቁ ናቸውና በቀላሉ ከጎኔ ላሰልፋቸው እችላለሁ  ብሎ  የሚነሳ ሃይል እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታወች ስላሉ ነው። በሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዉስጥ ያሉ ሰዎች ግን አንጃ መፍጠር ሊያስቡ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር ቢችልም አይሞክሩትም ፤ ምክኒያቱም በቀላሉ በጸጥታ ሃይሉ ሊጨፈለቁ እንደሚችሉ በሚገባ ይረዳሉና ። ወጣም ወረደ ግን በጸጥታ ሃይል ጡንቻ ተመክቶ ስልጣን  ላይ ተንጠላጥሎ ለመቀጠል መሞከር ለጊዘው ካልሆነ በስተቀር እንደማያዛልቅ ሊረዱት የሚገባቸው እነዚሁ የህወሃት ሰወች ነበሩ። ምክንያቱም በጸጥታ ሃይል ብቻ ህዝብን አፍኖ መግዛት ቢቻል ኖሮ ደርግ ለዘልአለም ስልጣን ላይ ሊቆይ ይችል እንደነበረ ከህወሃት ሰዎች የበለጠ ሊረዳው የሚችል አካል አልነበረምና ነው። ይልቁንም ሁሉም የጸጥታ ሃይሎች ማለትም የመከላከያ ሰራዊቱ፣ የደህንነት አገልግሎቱና  የፖሊስ ህይሉ ሁሉንም በሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተመጣጣኝ ሁኔታ እንዲወክሉ የሚደረግበት ሁኔታ ቢፈጠር የህዝብን አመኔታ በቀላሉ ማትረፍ ይቻል ነበር።  ይህ ደግሞ እዛው ሳለ ህወሃት ዉስጥና በዙሪያው ያሉ በትምክህት የተወጣጠሩ ሰወችን ጡንቻ የማላላት ሃይሉ ከፍተኛ ስለሚሆን እኩልነትንና እኩል ተጠቃሚነትን ለማስፈን የተመቻቸ መደላድል መፍጠሩ አይቀርም።  ከዚህ ባላፈ ደግሞ ህዝቡ ጩሖቴና ድምጼ ተሰማ የሚል ስሜት ስለሚያድርበት አብሮነቱና አንድነቱ እየተጠናከረና እየጎለበተ የሚሄድበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችል ነበር።

ሶስተኛው የኢህአዴግ ኢ-ህገመንግስታዊነት ማሳያ ደግሞ እኩል ተጠቃሚነትን በሚጻረር መልኩ የህወሃት ሰወች ኢኮኖሚዉን ለመቆጣጠር የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ያሉ መሆኑ ነው። የህወሃት ሰወች ኢኮኖሚውን በሞኖፖሊ ለመያዝ እየተጠቀሙበት  ያለው ኤፈርት (Effort) የተቋቋመው እነሱ እንደሚሉት ከዉጭ በተገኘ ድጋፍና ከኮንሰርት በተገኘ ገንዘብ ሳይሆን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከባንክ እና ከህብረት ስራ ማህበራት በተዘረፈ ገንዘብና ንብረት እንደሆነ በወቅቱ ፋይናንስ ዉስጥ ይሰሩ የነበሩ የራሳቸው ታጋዮች ሞቅ ሲላቸው በኩራት ይናገሩታል። ከዚሁ ጋ በተያያዘ ሊነሳ የሚገባው ደርግ ባዶ ካዝና ነው ያስረከበን የሚሉት ጉዳይ ነው።  በርግጥ ደርግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያራቆተ መሆኑ ላይ መግባባት ይቻላል። ይሁንና ባዶ ካዝና እንዲቀር ያደረጉት የህወሃት ሰዎች  በየደረሱበት ተሽቀዳድመው ባንኮችን ይዘርፉ የነበረ በመሆኑ ነው። ያም ሆኖ ግን  እነዚህ የህወሃት ሰዎች  ቅን የሆነ አስተሳሰብ ያላቸው ቢሆን ኖሮ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እኩል  በሆነ መንገድ  እንዲጠቀሙ ሁሉንም የልማት ድርጅቶች (Endowments) ተብለው የሚጠሩትን አንድ ላይ በማምጣት ባገር አቀፍ ደረጃ አንድ የልማት ድርጅት (Endowment) አቋቁሞ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ በእድገት ክፍተት ያለባቸዉን አከባቢወች እንዲደግፍ ሁኔታዉን ማመቻቸት በተገባው ነበር።

ባጠቃላይ የኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ህገመንግስታዊነት ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይህም ማለት ኢህአዴግ ህገመንግስቱ እንዲጸድቅ አደረገ እንጂ በተግባር ግን ሲያከብረው፣ ሲያስከብረው፣ ሲገዛበት፣ ሲፈጽመው እንዲሁም ሲያስፈጽመው አልታየም። በተቃራኒው የህገመንግስቱ ጠላቶች ኢህአዴግ ራሱና እርሱ የሚመራው መንግስት እንደሆኑ በድፍረት መናገር ይቻላል። በሌላ አነጋገር በኢህአዴግ ዘመን በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ህገመንግስትን መጣስና ሲህተቶችን መስራት እንደመርህ (principle) ህገመንግስትን ማክበር፣ መፈጸም፣ ማስፈጸምና ትክክለኛ ነገር መስራት ደግሞ እንደ ልዩነት (exception)   ተደርጎ እየተወሰደ ይገኛል።

የኢህአዴግ መገለጫ  ይህ ሆኖ እያለ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግን ኦህዴድ (OPDO) ባልተለመደ ሁኔታ  ወደመርህ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴና ህገመንግስታዊነት ጎዳና የገባ ይመስላል። በኦህዴድ ረገድ ይሀን ለማለት የሚያስደፍረው የህገመንግስት ይከበር ጥያቄ እያነሳ ያለ በመሆኑ ነው። ። በዚህ ዙሪያ ሊነሳ የሚችለው አንደኛው ጉዳይ በቅርብ ጊዜ በኦሮምያ ክልል ተከስቶ በነበረ የጽጥታ መደፍረስ  ሁኔታ  መከላከያ ሰራዊቱ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዉን ጥሶ ያለክልሉ ፈቃድ ዘው ብሎ በገባበት ውቅት ተቃውሞ ያነሳ መሆኑ ነው። መከላከያ ሰራዊቱ ይህን ያደረገው በቅን ልቦና ነው የሚል መከራከርያ ቢቀርብ እንኳን በኦህዴድ የሚመራው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያነሳው ተቃዉሞ ህገመንግስት ይከበር ከሚል መርህ የተመሰረተ ነው። ይህን በተመለከተ ህገመንግስቱ የማያሻማ ድንጋጌ አስቀምጧል። ይሄዉ ህገመንግስቱ በአንቅጽ 51 ንኡስ ቁጥር 14 መሰረት በግልጽ እንዳስቀመጠው የፌዴራል መንግስቱ “ከክልል አቅም  በላይ የሆነ የጽጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሃገሪቱን የመከላከያ ሃይል ያሰማራል” ይላል:: ከዚህ አንጻር ታድያ ህገመንግስቱን እያስከበረ ፣ እያከበረና በሱም እየተገዛ ያለው ማን ነው? ኦህዴድ ነው ወይስ በህወሃት ሰዎች የሚሽከረከረው የመከላከያ ሰራዊቱ? መቸም ትክክለኛ አእምሮ ያለውና የሚያገናዝብ ሰው  በኦህዴድ የሚመራው የክልሉ መንግስት ተቃዉሞ ህገመንስታዊ አልነበረም ሊል የሚችልበት መሰረት ሊኖረ አይችልም። ለዚህም ነው ታዲያ ኦህዴድ በህገመንግስታዊነት ጎዳና እየተራመደ ይሆን? የሚል አወንታዊ ጥያቄ እየተነሳ ያለው።

ሌላው ኦህዴድ በህገመንግስታዊነት ጎዳና ላይ ጉዞ ጀምሮ ይሆን? የሚያስብለው ጉዳይ  ደግሞ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በዜግነታቸው አድሎ ሳይደረግባቸው በኩልነት የመጠቀም እድሉ ይሰጣቸው የሚል አቋም መያዙና ለተግባራዊነቱም እየተንቀሳቀሰ ያለ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ ኦህዴድ በጣም አምርሮ እየታገለው ያለው ህገወጥ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ (Controband) እና የማፊያ አይነት እንቅስቃሴወች ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ እንቅስቃሴወች እኩል ተጠቃሚነትን መጻረር ብቻ ሳይሆን አገር የማፍረስም ሃይል አላቸው። እንደዉም አንድ ቡድን በተለይም ደግሞ መከላከያ ዉስጥ እና ጉምሩክን ጨምሮ በሌሎችም መስርያ ቤቶች  ያሉ የህወሃት ሰዎች በኔትዎርክ በመተሳሰር  ከሌላው በላይ እኩል በመሆን ህገወጥ በሆነ መንገድ ራሳቸዉን እያበለጸጉ መሆኑ ኢ-ህገመንግስታዊ ነዉና ይታረም/ይስተካከል እያለ ነው ያለው ኦህዴድ። ከዚህ በላይ ኦህዴድ በህገመንግስታዊነት ጎዳና ጉዞ  ጀመረ እንዴ ብሎ አወንታዊ ጥያቄ ማንሳት የሚያስችል ፍሬ ነገር ይኖር ይሆን?

ኦህዴድ እያነሳው ያለው ሶስተኛው የህገመንግስታዊነት መገለጫ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀሳቦች እኩል የመንሸራሸር ህገመንግስታዊ መብታቸው ይከበር የሚል ነው። በኦህዴድ አገላለጽ “እንደነብር ዥንጉርጉር” የሆነው የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተሳሰብ ህገወጥ የሆነ ገደብ ሳይጣልበት በነጻ ይፍለቅና በዙርያው የሚሰባሰቡ ዜጎች ደግሞ በፖለቲካ ፖርቲነትም ይሁን በሌላ ህጋዊ አግባብ ተደራጅተው የመንቀሳቀስ፣ በነጻ የመምረጥና የመምረጥ   መብታቸው ይከበርላቸው የሚል ነው። ህገመንግስቱም እኮ ከዚህ ዉጭ የሚለው ነገር የለዉም። ይህ ከሆነ ዘንዳ ታዲያ ኦህዴድ በህገመንግስታዊነት (constitutionalism)  ጎዳና ጉዞ ጀመረ እንዴ?  ብሎ  አወንታዊ ጥያቄ ማንሳት ምን ያሳፍራል?

ከኦህዴድ ህገመንግስታዊነት ጉዞ መጀመር ጋ በተያያዘ ብዙ ነገር ማንሳት ይቻል ነበር። ይሁን እንጅ ማንዛዛት ሊሆን ስለሚችል በዚሁ ቢበቃ የመረጣል። ይልቁንም ኦህዴድ የጀመረው የ ህገመንግስታዊነትና የመርህ ጉዞ የተሟላ ቁመና እንዲኖረው ጥንቃቄ ማድረግ ያለበትን የተወሰኑ ጉዳዮች አንስቶ መደምደም የበለጠ አስተማሪ ይሆናል። ኦህዴድ ሊያስተካክለው የሚገባው አንደኛውና ትልቁ ጉዳይ ከብሄርተኝነት ጋ ያለው የተዛባ እይታ ነው። ባንድ ወቅት አቶ ለማ መገርሳ ብሄርተኝነት ችግር እንደሌለው ሲናገሩ ተደምጠዋል። እንደዉም በሳቸው አገላለጽ ብሄርተኝነት መጎልበትና መጠንከር ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ነው የተቀመጠው። እዚህ ላይ አቶ ለማ  ሊገነዘቡት የሚገባቸው ቁምነገር ያለ ሲሆን ይሀዉም  ሁሉም አይነት ብሄርተኝነት  ገንቢ መሆኑን ለማመን አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ብሄርተኝነትም እንዲኖር ካስፈለገ ዴሞክራሲአዊ ብሄርተኝነት (Democratic Nationalism ) መሆን የሚገባው እንደሆነ በጽናት  ማመን ያስፈልጋል።  ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሲባል የራስንና የቡድንን ጥቅም ማስከበርና ለሱም መታገል ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ባልተናነሰ መልኩ ለሌሎች መብት መከበርም መታገልና መዋድቅ ማለት ነው።  ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ብሄርተኝነት ደግሞ ጥበትን፣ ስግብግብነትን፣ ሽፍትነትንና በህግ ያለመገዛትን ሊያስከትል ስለሚችል ኦህዴድ አደጋዉን በደንብ ተረድቶ በማያወላዉል መንገድና በጽናት  ሊታገለው ይገባል። 

ሁለተኛው ኦህዴድ ሊጠነቀቅበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ በህዝብ ድጋፍ ሰክሮ መርሁን እንዳይስት ነው። ኦህዴድ ግንባር ቀደም የሆነ መሪ ድርጅት ሁሉ ከስሜታዊነት የጸዳ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት። ይህም ማለት በጭፍን ድጋፍም ይሁን በጭፍን ተቃውሞ ላይ ተመስርቶ የሚወሰድ እርምጃ ወዳልተፈለግ አቅጣጫ ሊያመራ እንደሚችል ተገንዝቦ ምንጊዜም ቢሆን  ረጋ ብሎ ማሰብና ዙሪያ መለስ ሁኔታወችን አይቶ መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን መረዳት ለነገ የማይባል ተግዳሮት መሆኑን  መረዳት መቻል ማለት ነው። ከዚሁ ጋ ተያይዞ ኦህዴድ ሊያስብበት የሚገባው ከማንም ጋ ያለው ግንኙነት መተክላዊ መሆን የሚገባው መሆኑን ነው። ይህም ማለት ማንኛዉም አይነት ትግል ሲደረግ ነጻ፣ ግልጽ፣ ከጥላቻና ቂም የራቀ መሆኑን በጽናት ማመን የሚገባው መሆኑን ነው። በተለይም አሁን ያለው ትዉልድ አባቶቹና አያቶቹ ባጠፉት ጥፋት ተጠያቅ መሆን እንደሌለበት ኦህዴድ በሚገባ ተረድቶ የሚመራዉን ህዝብም እንዲረዳው ማድረግ ይጠበቅበታል። መቸም ቢሆን ያንድ ሰው ጥፋት ወደሌላ መተላለፍ አይችልም፤ guilt is not transferable  እንድሚሉት አይነት ፈረንጆቹ። በተመሳሳይ ሁኔታም አሁን ያሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የህወሃት ጥገኞችና ገዢ መደቦች በሚያደርሱት በደል ሌላዉን የትግራይ ንጹህ የሆነ ህዝብ በጅምላ ማዋከብ ተገቢ እንዳልሆነ ተረድቶ ኦህዴድ ቁርጠኛ የሆነ ትግል ማድረግ ያስፈልገዋል።

በመጨረሻም ኦህዴድ ለምን የኦሮምኛ ቋንቋን የፈደራል ቋንቋ እንዲሆን እንደፈለገ በደንብ ሊያስብበት ይገባል። አማርኛም ቢሆን እኮ አሁን የስራ ቋንቋ የሆነው በታሪክ አጋጣሚ በተከሰተ ሁኔታ ባብዛኛው ኢትዮጲያዊአያን ስለሚነገር ነው። ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ደግሞ ኦህዴድ በሚገባ ያቀዋል። በወቅቱ የነበሩት ገዥ መደቦች የፈጠሩት እንጅ ሌላ ምንም ምክኒያት አልነበረዉም። አሁን ታዲያ ኦህዴድ የኦሮምኛ ቋንቋ የፈደራል የስራ ቋንቋ ይሁን ብሎ ሲነሳ ገዥ መሆን ፈለገ ወይስ ሌላ አሳማኝ ምክኒያት አለው? ይህም ሆኖ ግን ጥያቄው መነሳቱ በራሱ ችግር የለዉም። ጥያቄው ደሞክራሲአዊ በሆነ መንገድ እስከቀረበና የኢትዮጵያ ህዝብም በህዝበ-ዉሳኔ ካረጋገጠው ኦሮምኛ ቋንቋ  የፌዴራል የስራ ቋንቋ ቢሆን ክፋት የለዉም። ከዚህ ባሻገር ግን ኦህዴድ የኦሮምኛ ቋንቋን የፌዴራል የስራ ቋንቋ ሆኖ በሌላው ላይ እንዲጫን የፈለገው የህዝብ ብዛትን መሰረት አድርጎ ከሆነ ግን ከጀብደኝነትና ከአምባገነንነት ዉጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። ይህ ካልሆነ ሌላው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ደግሞ የአማርኛ  ጥላቻ፤ ትንሽ ገፋ ከተደረገ ደግሞ ከኢትዮጵያ ለመነጠል ቅድመ ሁኔታን ማመቻቸት እንደሆነ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላልና ጉዳዩን በአንክሮ ማጤን እጅግ በጣም ጠቃሚ ይሆናል።