ባህርዳር እና ጎንደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ የስራ አድማ አድርገዋል

.አባይ ሚዲያ ዜና 

በፖለቲካ አመለካከታቸው መንግስት ያሰራቸውን ሰዎች እንዲፈታ እንዲሁም አገዛዙን ለመቃወም በአማራ ክልል በየካቲት 12 ቀን 2010ዓ.ም የስራ ማቆም አድማ ተደርጎ ውሏል።

የስራ ማቆም አድማው ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ እየተነገረ ሲገኝ መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት በደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ እንዲህ አይነት የተቋውሞ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ክልክል መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል።

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በየእስር ቤቶቹ እየተሰቃዩ ያሉትን የኦሮሞ ተወላጆችን ነፃ ለማስለቀቅ በመላው የኦሮሚያ ተደርጎ የነበረው የስራ ማቆም አድማ መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት በርካታ እስረኞችን ለማስፈታት እንደቻለ ይታወሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ በየካቲት 12 ቀን 2010ዓ.ም በአማራ ክልል የተጀመረው የስራ አድማ በጎንደር፣ በደብረታቦር እና በባህር ዳር ከተሞች እንደተደረገ ተዘግቧል።

የስራ ማቆም እና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማውን ሃላፊነቱን ወስዶ የጠራው ባይገለፅም በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች አድማው እንዲደረግ ጥሪ ሲደረግ እንደነበረ ይታወሳል።

ለሶስት ቀናት ይቆያል የተባለውን የስራ ማቆም እና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማን ተከትሎ በከተሞቹ ሱቆች እና የንግድ ተቋማት ተዘግተው እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።