የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት በተቋቋሙት የኮማንድ ፖስት አባላት ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ታወቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
አቢሰሎም ፍሰሃ

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የአገሪቱን ሕዝቦች በወታደራዊ ኃይል ጨፍልቆ ለመግዛት የመጨረሻው የሆነውን ምርጫ በመጠቀም  የህወሓት ጄኔራሎች የሚመሩት ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሕዝብን ለመግደል፣ ለመጨፍጨፍ፣ ለማሰርና ለማንገላታት በአማራ ክልል በተንቀሳቀሰው የህወሓት የኮማንድ ፖስት አባላት ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮች ከየካቲት 16-17 ቀን 2010 ዓ.ም በተከታታይ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡

በዚህም መሰረት የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 2:00 ሰዓት በሰሜን ጎንደር ዞን በለሳ ወረዳ አርባያ ከተማ የኮማንድ ፖስት ምክትል አስተባባሪ መላኩ የተባለውን ታጣቂ በመግደል ትጥቁን ወርሰው አርበኞቹ በሰላም ወደቦታቸው መመለሳቸውንና ከዚያ ቀን ጀምሮ የኮማንድ ፖስቱ እንቅስቃሴ መገታቱን የዜና ምንጫችን ገልጿል፡፡

የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን አርማጮሆ ወረዳ ጃንሱማ ቀበሌ የተንቀሳቀሰው የአርበኞች ቡድን፣ የህወሓት ኮማንድ ፖስት ኃይል አዛዡን፣  ሻምበል አበባውን፣ ገድለው የእሱን አባል  ምክትል መቶ አለቃ በሪሁን ንጋቱን በማቁሰል በሰላም ወደ ቦታቸው መመለሳቸዉን የዜና ምንጫችን አረጋግጧል።

እንዲሁም የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 3:40 ሲሆን በሰሜን ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ ጫሂት ከተማ የወረዳውን የኮማንድ ፖስት ማዘዣ ጣቢያውን አጥቅተው በኮማንድ ፖስት አባላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ ኮማንድ ፖስቱ ቦታውን ለቆ መውጣቱንና ከ1:00 ሰዓት በላይ በቆየው የተኩስ ልውውጥም የህወሓት የፀጥታ ኃይሎች ራሳቸውን ለማዳንና ለመሰወር ሲሯሯጡ መታየታቸውን የዜናው ምንጭ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በትናንትናው ቀን የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ጎንደር ከተማ አዘዞ ወታደራዊ ካምፕ የሰሜን ቀጠና የኮማንድ ፖስቱ ዋና ማዘዣ ጣቢያና የቀጠናው የኮማንድ ፖስት አዛዥ የህወሓቱ ጄኔራል ሲሳይ ያለበትን በዋነኛነት በኮማንድ ፖስቱ የሚያዙ ሰዎችን ማሰሪያና ማሰቃያ ክፍል አርበኞች ሰብረው በመግባት ከ2:00 ሰዓት በላይ የቆየ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በዚህ ዘመቻ አርበኞች ቦታውን ለቀው ከወጡ በኋላ የህወሓት መከላከያ አባላት እርስ በርስ ሲታኮሱ በማንጋታቸው በአካባቢው የኮንደሚኒየም ቤቶች የሚኖሩ ኗሪዎች በነበረው የተኩስ ልውውጥ እንቅልፍ አጥተው ማደራቸውም ተገልጿል። በዚህ የእርስ በርስ የተኩስ ልውውጥ የህወሓት ወታደሮች እንደ መትረየስ እና ድሽቃ አይነቶች የቡድን መሳሪያዎች በመጠቀማቸው በተኩሱ የአካባቢው ኗሪዎችን ሲሸበሩ ማደራቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀ መንበር ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን “ያለ የሌለ ሀይል አሰባስበን ይህን አዋጅ እንሰብረዋለን” በማለት በቅርብ የተናገሩትን በመጥቀስ የአርበኛ ግንቦት 7 ምንጮች አሁንም በተከታታይ  ሕዝባችንን ከግድያ፣ ከጭፍጨፋ እና ከእስር ለመከላከል አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፈል የተዘጋጀን መሆናችንን እንገልፃለን ብለዋል፡፡