በሶማሊያ በፍተሻ ጣቢያ ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ደረሰ

አባይ ሚዲያ ዜና

በሶማሊያ በደህንነት ፍተሻ ጣቢያ አጠገብ በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ።

ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በ15 ኪሜ ርቀት በሚገኝ የፍተሻ ጣቢያ ላይ የተፈጸመው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በደረሰበት ወቅት የጥይት ተኩስ ሲሰማ እንደነበረም የአይን እማኝ ለሮይተርስ ተናግሯል።

ጥቃቱን በተመለከተ ምርመራ ለማድረግ የተገኙ አንድ የፖሊስ አባል በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ ገልጸው የጉዳቱን መጠን ተገቢው ምርመራ ከተደረገ በኋላ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በፍተሻ ጣቢያው ለተፈጸመው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የአልሸባብ ድርጅት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አልሸባብ በሞቃዲሾ ባደረሰው የአጥፍቶ መጥፋት የቦምብ ጥቃት ወደ 45 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ይታወሳል።