ፕሬዝዳንት ፑቲን በየትኛውም አቅጣጫ የሚገኝ ቦታን የሚደመስስ የኑክሊየር ጦር አገራቸው ማምረቷን ተናገሩ

አባይ ሚዲያ ዜና

በቅርቡ የሚደረገውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሰፊ እንደሚያሸንፉ የሚጠበቁት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየትኛውም የአለም አቅጣጫ የሚገኝ ቦታን መምታት የሚያስችል የኑክሊየር የጦር መሳሪያ አገራቸው ማምረቷን ተናገሩ።

በየትኛውም የአለም አቅጣጫ የሚገኝን ቦታ መምታት የሚያስችለው የኑክሊየር ጦር መሳሪያው በምንም መልኩ ሊጨናገፍ እንደማይችልም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ በሞስኮ በሚገኘው የኮንፈረንስ አዳራሽ ለተሰበሰቡ ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግራቸው ምእራባውያኑ አገራቸውን ወደ ኋላ ለማስቀረት ሲያደርጉ የነበረው ሙከራ እንደከሸፈባቸው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን አገራቸው በዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ በመጠቀም የፈበረከቻቸውን የኑክሊየር እና የአሃጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን በፕሮጀክተር እና በስክሪን በመታገዝ ለኮንፍረንሱ ታዳሚዎች  ሲያሳዩ አዳራሹ በጭብጫባ በተደጋጋሚ ሲደምቅ ታይቷል። ፕሬዝዳንቱ አገራቸው ስለደረስችበት የጦር ቴክኖሎጂ ገለጻቸውን በሚሰጡበት ወቅትም በአዳራሹ የተገኙ ተሰብሳቢዎች ከመቀመጫቸው በመነሳት ሲያጨብጭቡ እና የሩሲያ ብሄራዊ መዝሙርም ሲሰማ እንደነበረ ተዘግቧል።

የሩሲያ አጋር ላይ የሚቃጣ የኑኩሊየር ጥቃት በሩሲያ ላይ እንደተቃጣ እንደሚቆጠር ያስታወቁት ፕሬዝዳንት ፑቲን ምላሹም በጣም ፈጣን እንደሚሆን እና ማንም በዚህ ጉዳይ አንዳች ጥርጣሬ እንዳይኖረው በማለት አስጠንቅቀዋል።

ዩናይትድ ስቴትስም ሆነ ምእራባውያን አዲሱን እውነታ መቀበል ግድ እንደሚላቸው በመግለጽ በአገራቸው ጉዳይ የሰጡት ገለጻም የቀልድ ሳይሆን የምር እንደሆነ ፕሬዝዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያ ያዘለ ጠጣር መልክትን አስተላልፈዋል።