‘የሩዋንዳን ጠባሳ ያየ በዘር የእሳት ፖለቲካ አይጫወትም (በፀሎት አለማየሁ )

0

ብልጥ ሰው ሁሉንም ስህተቶች ለመስራት በቂ ጊዜ ስሌለለው ከሞኞች ይማራል የሚል ብሂል አለ። ስህተቱ በግልም በቡድንም ወይንም በሀገርም ደረጃ ሊሆን ይችላል። ብልጥ ከሆንን ያንን ስህተት ላለመድገም እንሞክራለን። በተለይም ደግሞ የስህተቱ መዘዝና የሚያስከትለው አደጋ በቀላሉ የማይድን ከሆነ። ለትውልድ የሚተርፉ ስህተቶችን አለማችን አስተናግዳለች። እንደ ኢትዮጲያዊያን ደግሞ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንማርበት የሚገባው የቅርብ ጊዜውን  የሩዋንዳ ስህተት ነው። ሩዋንዳ ለጊዜውም ቢሆን የተረጋጋችና ዕርቅና ሰላም የወረደባት አገር ብትመስልም ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ ከሚችል የተዳፈነ ገሞራ ጋር የሚያመሳስሏት ብዙዎች ናቸው። በተለይም ለደረሰው ዕልቂት ዋና መሃንዲስ ሆኖ ከጀርባ የጥላቻውንና የጭፍጨፋውን ዕቅድ ሲያቀነባብር የነበረው የአናሳዎቹ ቱትሲዎች መሪ ፖል ካጋሜ ያገሪቱ ርዕሰ ብሄር ሆኖ መቀመጡ የሩዋንዳን ፖለቲካ በቀል ያረገዘ ፖለቲካ ነው ይሉታል። ዋናው ነጥብ ግን 1 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከምድረ ገጽ ባሰቃቂ ሁኔታ መጥፋቱ ነው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ታግዞ ለ6ሚሊዪን አይሁዳዊያን ሞት መሳሪያ ሆኖ ካገለገለው የናዚ ጀርመኖቹ የጋዝ ማሽን ይልቅ ጥንታዊዉ ቆንጨራ እጅግ ፈጣንና የተሳለጠ ውጤት ማምጣቱ ይታወቃል። ብልጦች ከሆንን ከሩዋንዳ ምን እንማራለን ነው ጥያቄው።

አንድ የመንግስት አወቃቀር በዘር ፣በብሄር ፣ በጎሳ፣ዘውግ እያለ ህዝቡን እንደፈለገ እየከፋፈለ፣ እየቆራረጠ እየበተነ አንዱ የተመረጠ ሌላው ላይ የሚያደርሰው ጫና፣ ጥቃት፣ መናቅ ፣መድፈርና የመብት ጥሰቶች ለገዥው መደብ ስልጣን ላይ ለተወሰነ እድሜ ተቆናጦ እንዲቆይ ሲያስችል ለሀገርና ለህዝብ ግን ከባድ የእልቂትና የሞት መሰረት ይሆናሉ።ሩዋንዳን ለከፋ መጨረሻ የዳረጋትም ይሄው ነበር። አገዛዙ ከቅኝ ገዢዎቹ ፈረንሳዮች የተረከበውን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በማስቀጠሉና እኩልነት፣ ነጻነትና ፍትህ መጥፋትን በማስከተሉ። ልሂቃኑ በዘረጉት የተዛባ ስርዓት ህዝቡ እርስ በርሱ ተላለቀ።ህጻናትን እሳት እንዳትነኩ ብለን ብናስፈራራቸውም አንዳንዴ እሳቱን ካልጨበጡ የማይማሩ እንዳሉም እናውቃለን። ከነሱ ጠባሳ ሌሎች ግን ሌሎች ይማራሉ። በተለይም ትኩስ ጠባሳ ከሆነ።

በሩዋንዳው የዕልቂት  ዘመን ከሞት ተርፋ የዓይን ምስክርነቷን የሰጠች አንዲት ያገሬው ዜጋ የጥላቻ መርዛቸውን ሲረጩ ስለነበሩት የሁቱ ሃይሎች ስትናገር “ ከቤታችን መውጣት እንድፈራ ይፈልጉ ነበር፣ ቤታችንን ቆልፈን፣ ልጆቻችንን ደብቀን በፍርሃትና በጭንቀት እንድንኖር ተመኙ፣ የኛ ፍርሃትና ጥላቻ የነሱ መደበቂያ ዋሻ ስለነበር ህይወትን ራሷን እንድንጠላት ነበር ዓላማና ፍላጎታቸው፣ ቱትሲዎችን እንድንጠላቸው ይፈልጋሉ፣ የሌላው ወገን ነው ስለዚህ መጥላት አለባቸሁ ይሉን ነበር፣ ከኛ በተለዩት ላይም ጥቃትና ግድያ እንድንፈጽም ያስገድዱን ነበር፣ እኛን መከፋፈልና ማጫረስ ነበር ፍላጎታቸው፣ ይህንን በወንድምና በእህቶቻችን ላይ አናደርግም ያሉትን ደግሞ ከጠላት የባሰ የውስጥ ጠላት ብለው የመጀመሪያውን ቆንጨራ አንገታቸው ላይ አሳረፉ፣ መሬቷ በንጹሃን ደም ጨቀየች፣ ቅንነታችንን፣ ደግነታችንንና ሰብዓዊነታችንን ከውስጣችን እንድናጠፋው ፈለጉ፣ ፍቅራችንን እንድንቀብር፣ብርሃናችንን እንድናጠፋ፣ ነገ የሚባል ነገር እንደሌለ ሰበኩን። አንድ ላይ የኖርነውን ህዝቦች የቤታችን አጥር ይለየን ይመስል፣ የያዙት መሳሪያ የመንፈሳችንን አንድነት ይሰብርና ያሸንፍ ይመስል፣ ብዙ ሞከሩ፡ የቻሉትን ያህልም አደረጉ። ያልገባቸው ነገር ግን የወንድሜ አንገት ሲቆረጥ የኔም እንደሚደማ አላወቁትም፣ ስለዚህ አንፈራም፣ አንጠላም፣ መቼም ዝም አንልም፣ ፍቅርና ህይወት ከኛ ጋር ናቸውና።” ትላለች።

የሩዋንዳን ጉዳይ በተለይ ልብ ልንለው የሚገባን አንድ ሌላ ወሳኝ ነገር አለ። የሩዋንዳ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎች በመሃንዲስነት በመሩት የዘር ዕልቂት ላይ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ በሚያሳዝንና በሚዘገንን ሁኔታ ካለቀ በኋላ ያገሪቱ ህገ መንግስት ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ሰው ሁቱ ወይንም ቱትሲ ብሎ ራሱን በብሄር ማንነቱ መግለጽ የለበትም። ሁሉም የሩዋንዳ ዜጋ ነው። ይህንን የማንነት ጉዳይ ተላልፎ ራሱን ሁቱ ነኝ ቱትሲ ነኝ ቢል በህግ ይቀጣል የሚል አዋጅ መደንገጉ ነው። ያንድን አገር ዜግነት ለማረጋገጥ ሩዋንዳ የግድ በዚያ አይነት ሁኔታ ውስጥ ማለፍ ነበረባት? ለማንኛውም ብልጦች ከሞኞች ይማራሉ ነውና የኢትዮጲያዊ ዜግነታችንን ዋጋ ሳናራክስና የህወሃት የዘር ቁማር ሰለባዎች ሳንሆን እንደ አንድ አገር ዜጎች እንተያይ።

በመሆኑም የጥላቻና የቂም በቀል ስብከትን ጆሮ አንሰጠውም ማለት አለብን። ጥላቻው ከየትም ወገን ይምጣ ከየት ኦይናችን ስርዓቱ ሕወሃት ላይ እንጂ ህዝብ ላይ እንዳይሆን አደራ። ኢትዮጲያን እስካሁን የጠበቃት የህዝቧ ጨዋነት፣ የመቻቻል ባህሉ እንጂ እንደ ህወሃቶች የጥላቻ፣ የመከፋፈልና የቂም ፖለቲካ ማዕበል ቢሆንማ ኖሮ ኢትዮጲያ የምንላት መርከብ ዱሮ ገና ተሰነጣጥቃ በሰመጠች ነበር።

ኢትዮጵያ የምትባለውን መርከብ ክፉኛ እያላጋት ያለው የፓለቲካ ሱናሜ የህወሃት ደንቆሮ ካፒቴኖች ወደማንፈልገው አቅጣጫ በማንፈልገው መንገድ እየወሰዱን መሆኑን እዚህ ላይ መዘርዘሩ ለቀባሪው ማርዳት ነዉ።

ስለ ህወሃት አንድ ነገር በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። መርከቡ እንደ ታይታኒክ ከበረዶ ግግር ጋር እንደሚላተምና ለሁሉም ተሳፋሪዎች ካፒቴኖቹን ጨምሮ አደጋ እንዳለው እያወቁም ቢሆን እኛ ያልነዳነው መርከብ አብሮን ይስጠም በሚል የአጥፍቶ መጥፋት አስተሳሰብ ውስጥ እንዳሉ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ይዘውን ሊጠፉ የተዘጋጁ  ሃይሎች ናቸው። ስለሆነም ከአጥፍቶ ጠፊ ጋር ስትታገል ጥበብ፣ ትዕግስት፣ ቁርጠኝነትና ከሁሉም በላይ ዋና መድረስ የምትፈልግበትን አቅጣጫና ቦታ እንዳትዘነጋ ያስፈልጋል።

እንደ አንድ ተቃዋሚ ሃይል ህወሃትን ለምንድነው የምታገለው ብለህ ራስህን ስትጠይቅ ቀድመው ወደ ጭንቅላትህ የሚመጡ የህወሃት ባህሪ መገለጫዎች አሉ። ዘረኝነቱ፣ ኢፍትሃዊነቱ፣ ጸረ-ኢትዮጲያዊነቱ፣ ጨለምተኝነቱ፣ ስግብግብነቱና የመሳሰሉት የሳጥናኤል ባህሪዎች ይታዩበታል። ይሄንን አልፈልግም።  እኔ የምታገለው ዘረኝነትን ለማጥፋት፣ ፍትህን ለመተግበር፣ ኢትዮጲያዊ አንድነትን በዲሞክራሲ መሰረት ላይ ለመጣል፣ አጥፍቶ መጥፋት ሳይሆን አልምቶ መልማትና የዕኩል ብልጽግናን ማየት፣ ከልክ ያለፈ ስግብግብነት የራስን ስጋዊ ፍላጎት ብቻ እንደ እንስሳ ከማርካት ያለፈ በእግዚአብሄር አምሳል ለተፈጠረ ክቡር የሰው ልጅ መንፈሳዊ ህይወት አይመጥንምና በልክ እኖራለሁ የሚል ጠንካራ አቋም መያዝ ያስፈልጋል።

ኢትዮጲያ የምትባለው መርከብ በውስጧ ያሉ ብዙ ህብረ ብሄሮችን ይዛ የምትጓዝ ናት። ሁሉም በዚህ መርከብ ውስጥ ያለ የተሳታፊነት ብቻ ሳይሆን የባለቤትነት ስሜትም ካለው ለመርከቧ ደህንነትና ሰላም መጨነቁ አይቀርም። በእኩል የባለቤትነት ስሜት ጉዞው ላይም ሆነ መዳረሻው ላይ የራሱ ሚና ይጫወታል።

ታይታኒክ ከበረዶው ግግር ጋር ተጋጭታ የታችኛው የመርከቧ ክፍል ሲሰነጠቅና ውሃ መሙላት ሲጀምር ከፍተኛ ነውጥና ውስጥ የነበሩ የሲቃ ድምጾች ይሰሙ ነበር። ሰዎች ህይወታቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ፣ በጨለማ ሲራኮቱ፣ ተስፋ በመቁረጥ ወደባህሩ እየዘለሉ ሲሰጥሙ የመርከቧ አናት ላይ ያለው ሳሎን ውስጥ የነበሩት ሃብታም ተሳፋሪዎች ሙዚቃ እየሰሙ፣ እየደነሱ፣ ፍቅር እየሰሩ አለማቸውን ይቀጩ ነበር። ታችኛው ክፍል የነበረው አስጨናቂ ሁኔታ፣ ሞትና የራስ ማዳን ግርግር ለላይኛዎቹ ሰዎች የተደበቀ ነበር።ውሃው ሞልቶ፣ መርከቧ መስጠምና የነሱም ተራ እስኪደርስ ድረስ። መጨረሻ የሆነውም ይኸው ነበር። ሰውም መርከቧም ላይመለሱ ባህር አዝቅት እስከዘላለሙ ተውጠው ቀሩ።

ወገኖቼ የታይታኒክ ዕድል እኛም እንዳይደርሰን እንጠንቀቅ። ወዳጅና ጠላት እንለይ። ስርዓትንና ህዝብን እንነጥል። አንዳንድ ጊዜ በህወሃት ተንኮልም ይሁን በሰዎች ከንቱነት፣ ዕብሪት፣ጊዜው የኔ ነው በሚል ማን አለብኝነት ስሜትና የመሳሰለው ክፉ ነገሮች ሲደረጉ ብታይም አስታውስ ይህንን ያደረጉ እከሌና እከሌ ናቸው የማለት አስተሳሰብን አዳብር እንጂ በፍጹም በጅምላ አትፈርጅ።ወያኔ/ህወሃት የሚፈልገው ይህንን ስለሆነ።ከዛ ሁሉ ዕልቂት በኋላ የሩዋንዳ ህዝብ ከነህመሙ፣ ከነቁስሉ፣ ከነፍቅሩ፣ ከነቅሬታው እየኖረ ነው። ደጋግሞ እንደሚባለው፣ መንግስት ያልፋል ህዝብ ግን ዘላለማዊ ነው።

ለኢትዮጵያውያን አዲስ የተስፋ ብርሀን አገኙ የሚያስብል የፖለቲካ ምህዳር እየተፈጠረ እና ከተጋረጠበት ከባድ የፖለቲካ ሱናሚ እየወጣ ነው ብለን እናምናለን ።የዘር ፖለቲካውን ህዝቡ በሚገባ ተረድቶ ፣ተከፋፍሎ ከመታገልና ከማታገል ይልቅ እንደ ኢትዮጵያዊነት ተሰባስቦ በአንድ ላይ በመሆን ነፃነትን ለማግኘት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተረድቷል።እነጌታቸው ረዳ እሳትና ጭድ ናቸው ሲሏቸው የነበሩት የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች መካከላቸው ላይ የነበረውን መሰናክል ቆራርጠው በመጣል በአንድነት የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከወዲያ ወዲህ በክብር ተቀባብለው እየዘመሩ ነው። ቄሮዎችና ፋኖዎቹ ደቡቦችም ከጎናችሁ ነን በማለት አጋርነታቸውን እየገለዱ ነው።ሕወሃት ለረዥም ዘመን የኔ ነው ብሎ ሲደበቅበት የነበረው ትግራይ ህዝብ የለም አትወክለኝም፣ ከቀረው ወገኔ ጋር አብሬ ብኖር ይሻለኛል እያለ ነው። ኦህዴድም አብዮታዊ እርምጃ በሚባል መልኩ ከብሄር ተኮር እሳቤ አልፎ አገራዊና ቀጣናዊ ስለሆኑ ጉዳዮች ሲመክርና ሁሉንም በውስጥም ያሉ ይሆን በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ኢትዮጲያዊያን ድርጅቶችን ለሰለጠነ የፖለቲካ ውይይት መጋበዙን ስንታዘብ በርግጥ የማታ ማታ አገራችንን ፈጣሪ እየታደጋት ነው ብለን በድፍረት መናገር የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በተለይም ደግሞ ሕወሃት የፖለቲካ መደራደሪያ አድርጎ ለረዥም ዘመን የተጠቀመበት የትግራይ ሕዝብ በተለይም ደግሞ ምሁራኑና አክቲቪስቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሕወሃት አይወክለንም፣ ከኢትዮጲያ ሕዝብ ጋር በአንድነት እንቆማለን፣ በትግራይ ህዝብ ስም መነገዱ ይብቃ ማለት መጀመራቸው በአማራውና በኦሮሞው መካከል እየጠነከረ የመጣው አይነት ቅርርብና መተማመን ከትግራይ ወጣቶችም ጋር እንዲሁ እንደሚሆን የሚያረጋግጥ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው ብለን እናምናለን። አብርሃ ደስታ ባንድ ወቅት እንዳለው የትግራይ ማህጸን የወለደው ህወሃትን ብቻ አይደለምና።ይህ ሁኔታ ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ለሚንቀሳቀሱ፣ዜግነትን ዋና መስፈርት ላደረጉ እንደ አርበኞች ግንቦት ላሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና በኢትዮጲያ አገራዊ ንቅናቄ ውስጥ ላሉት አካላት ትልቅ ብርታትና ድጋፍ ሲሆን በብሄር ስም ድብቅ ፍላጎታቸውንና አላማቸውን ለማስፈጸም ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ግለሰቦች ደግሞ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ራሳቸውን እንዲመረምሩ ጥሩ ማሳያ መስታወት ሁኗል ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አስተሳሰብ ካላቸው የህወሃት ኢሊት ባለስልጣናትና ተጠቃሚዎች እጅ ወጥቶ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት፣ በህዝብ የተመረጠ መሪና ፓርቲ ብቻ የመንግስትን ስልጣን የሚይዝበት አሰራር መዘርጋት ይኖርብናል።ባጭሩ አዲስ የፖለቲካ ባህል በህዝብ ስነ ልቦና ውስጥ ማሰረጽ ይኖርብናል።በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የሚደረገው የልጅና የእንጀራ ልጅነት ስሜት ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ለሁሉም ዜጋ እኩል ያላትን ሳትሰስት የምትሰጥ የሁሉም እናት የሆነች ኢትዮጲያን መፍጠር ለነገ የማንለው የሁላችንም የቤት ስራ ነው። ይህንን በብቃትና በጽናት ከተወጣን በርግጥም ከሩዋንዳ ስህተት ተምረናል ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራ ትኑር ።