ነጻነቴን ስጠኝ ወይንም ደግሞ ሞቴን ወዲህ በል! ብቸኛው የነጻነት መንገድ! (በፀሎት አለማየሁ )

0

ያሁን ዘመን ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ ዘርማዎችና ነብሮች በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውንና ታሪካዊ ንግግር ያደረገውን አሜሪካዊዉን ወጣት ፓትሪክ ሄንሪን ያስታውሱናል። በአሜሪካ ግዛት የቨርጂኒያ ስብሰባ ተብሎ በሚታወቀው መድረክ ላይ ህዝቡ ያቀርብ ለነበረው የመብትና የነጻነት ጥያቄ ፓትሪክ ሄንሪ የተባለ ወጣት አሜሪካዊ ባጭርና ግልጽ በሆነ ቋንቋ የህዝቡን ስሜትና ሃሳብ በንግግሩ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር  ነጻነቴን ስጠኝ ወይንም ደግሞ ሞቴን ወዲህ በል! ይህም አስደማሚ፣ ወኔ ቀስቃሽ የሆነና ለትውልድ ሁሉ የተላለፈ ንግግር አሜሪካንን ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ በማውጣት ትግል ውስጥ ታላቅ ሚና ተጫውቷል ይላሉ የታሪክ ጸሃፊዎች።

የኢትዮጲያ የወደፊት ታሪክ ጸሃፊዎች፣ ባለቅኔዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የኪነት ባለሙያዎች ሁሉ ተመሳሳይ የሆነ ገድላቸውን የሚዘክሩላቸው ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ ዘርማዎችና ነብሮዎች ተወልደዋል። ነጻነት ወይንም ሞት! ያሉ ወጣቶች። የህወሃት አገዛዝ ይብቃ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሽግግር መንግስት ይቋቋም፣ ብሄራዊ ዕርቅና መግባባት ይፈጠር፣ ህዝብ የመረጠው መንግስትና መሪ ያስተዳድረን ብለው የሚታገሉና ለዚህም ህልም ዕውን መሆን ውድ ህይወታቸውን እየገበሩ ያሉ የዘመኑ ፓትሪክ ሄንሮዎች። ወጣቶቹ ለዚህ የነጻነት ጥያቄ ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ያለፉት 3 አመታት በቂ ምስክሮች ናቸው። ለመናገር፣ ለመሰብሰብ፣ ለመጻፍ፣ የጄኔራል ሳሞራንና እሱ የሾማቸውን አገልጋዮች በጎ ፈቃድ አንጠብቅም እያሉ ነው። እንደ ሰው፣ እንደ ዜጋ፣ እንደ ኢትዮጲያዊ የወያኔው ሕገ መንግስት ራሱም ቢሆን  ያስቀመጠውን በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ የመቃወም የዜግነት መብትና ግዴታቸውን እየተወጡ ነው።  ያስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያንን የማይፈቅድ ከሆነ ደግሞ እንደ ፓትሪክ ሄንሪ ነጻነታችንን ስጡን ወይንም ደግሞ ሞታችንን ወዲህ በሉ እያሉ ነው። በነጻነት ለመኖር የማንንም ፈቃድ የማይጠይቁባት አዲስ ኢትዮጲያን ለመፍጠር እየታገሉ ነው።

ለዚህም ነው ወያኔ/ህወሃት ደጋግሞ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም፣ በጅምላ እስከ 25 ሺህ በላይ ወጣቶችን በመጀመሪያው ዙር አዋጁ ቢያስርም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የወደፊቱ ኢትዮጲያ ተስፋ የሆኑ ወጣቶችን ባደባባይ ቢቀጥፍም፣ ነፍሰጡሮችንና አዛውንቶችን ቢያዋርድም፣ የሃይማኖት በአላትን በማርከስ ታቦት ፊት ሬሳ ቢረፈርፍም፣ በአዋጅ ስም የዜጎችን ቤትና ንብረት ቢዘርፍም፣ ሚሊዮኖችን ቢያፈናቅልም፣ ሴቶችን በየመንገዱና በየጫካው ቢደፍርም፣ ከሰማይ በታች ያለ ምንም አይነት ሳጥናኤላዊ ጥላቻ የተሞላበት ግፍ  በገዛ ወገኑ ላይ ቢፈጽምም፣ ወጣቶቹን ከአቋማቸው ምንም ሊነቀንቃቸው ያልቻለው። እንዳውም የአገዛዙ ኋላቀር አስተሳሰብና ጭካኔ ቄሮዎቹን፣ ፋኖዎቹንና ዙርማዎቹን ይበልጥ እንዲያመሩ፣ ይበልጥ እንዲደራጁ፣ ይበልጥ በትግላቸው እንዲጸኑና የሕወሃት ወያኔን ጨቋኝ አገዛዝ ከስር መሰረቱ መንግለው እንዲጥሉ እልህ አፍላቂ ብርታት ሆኗቸዋል። ለዚህም ነው ሁለተኛው ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀ ማግስት በወልቂጤ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በደብረታቦር፣ በነቀምቴ፣ በደምቦዶሎ፣ በአምቦና በወሊሶ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ነጻነት ስጠኝ ወይንም ደግሞ ሞቴን ወዲህ በል ብለው የሞትን መራር ጽዋ በድፍረት እየተጎነጩ ያሉት። ከአስፈሪው የአጋዚ ጥይት ይልቅ ነጻነታቸውን አክብረው ባመኑበት እየወደቁ ያሉት። በኢትዮጲያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የነኚህ ወጣቶች ሚና መቼም የማይረሳ ገድል ሆኖ ይኖራል። ክብርና ምስጋና ለቄሮዎቹ፣ ለፋኖዎቹ፣ ለዘርማዎቹና ለነብሮቹ ይሁን!

በሳጥናኤላዊ ጥላቻና ፍራቻ የተለከፈው ሕወሃት አሁንም ድረስ እያፈጠጠና ገሀድ እየሆነ ያለውን የኢትዮጲያ ሕዝብ ጥያቄ ለመስማት ልቡ ደንድኗል፣ ጆሮው ተደፍኗል፣ አይኑ ታውሯል፣ ህሊናውም ተሰልቧል። 26 አመታት ሙሉ አቅፈው ደግፈው ለዚህ ያደረሱት ምዕራባዊያን ወዳጆቹም ፊት ነስተውታል። ጌም ኦቨር ፣ ጨዋታው በቃ እያሉት ነው። ሕወሃት አሁን ምንም የቀረው ነገር የለም ከምላሱና ከጥይቱ በቀር። እነኚህን ደግሞ አዋጅ መለፈፊያና ሕጻናትን መግደያ አድርጓቸዋል። ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጠረው የህዝብ ሕጋዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ በመፍታት ብቻ እንጂ በጥይትና በሽብር እንደማይሆን ራሱ ህወሃት አሸንፎት ከመጣው የደርግ አገዛዝ ውድቀት ለመማር ያልቻለ የመንፈስ ድኩማኖችና የመሃይሞች ስብስብ ሆኗል ህወሃት ማለት። መንግስት በህዝብ ላይ መተኮስ ከጀመረ ውድቀቱን አፋጠነ የሚለው አነጋገር በወያኔ ላይ በግልጽ እየሰራ ነው። የህወሃት ጸረ ህዝብ፣ ጸረ-ዲሞክራሲና ጸረ-ፍትህ ሃይሎች የመረጡት የአጥፍቶ መጥፋት መንገድ በርግጥም መጥፊያቸውን እያፋጠኑ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል። ይህንን ዕውነት ደግሞ ወያኔ/ህወሃት ሰሞኑን ያወጣውን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በደምቢዶሎና በነቀምት ያፈሰሰውን የንጹሃን ደም ማየቱ በቂ ምስክር ነው።

ይህንን ሁሉ አረመኔአዊ ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ደግሞ ያገዛዙ ልሳን በሆኑት ኢቢሲና ፋና ራዲዮ በሰበር ዜና እወጃው የጸጥታ ሃይሎች ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ እያደረጉ ነው ካለ በኋላ ይቀጥልናም እነኚህ የጥፋት ሃይሎች ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ አስፈላጊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ተወስኗል ይለናል። እስከዛሬ እንደጎርፍ ያፈሰሰው ምን ነበርና ነው አሁን አስፈላጊ ዕርምጃ በሚል ስም የመግደል ነጻ ፈቃድ ለአጋዚ ጦር የሰጠው ? በውነት ወያኔ እስካሁን በህዝባችን ላይ ካደረሰው ግፍና ከፈጸመው ወንጀል በላይ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ ምን ሊያደርስበት ይችላል? ሰውን ሰው የሚያሰኙትን ነገሮች ሁሉ ነጥቆታል። ፍቅሩን፣ ተስፋውን፣ ደስታውን፣ ነጻነቱን፣ ማንነቱን ሁሉ በወያኔ ህወሃት የተነጠቀ ወጣት ትውልድ ነው። ምንም የቀረው ነገር የለም። ከስልጣን ወንበሩ የዘለለ ለምንም ነገር ትርጉም በሌለው የዱርዬዎች ስብስብ በሆነው ህወሃት የጨለማ ህይወት እንዲገፋ የተፈረደበት ትውልድ ሆኗል (ወጣቱ)። ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲያ ሕወሃት የአዋጅ መዓት ቢደረድር፣ ቢዝትና ቢያስፈራራ፣ ፓርላማውም ይህን አዋጅ ቢያጸድቅም ባያጸድቅም የመጨረሻ መዳረሻችን ከሆነው የብሄራዊ መግባባት፣ የሽግግር መንግስት መመስረትና ለዕውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከምናደርገው ትግል ወደኋላ የሚጎትተን ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል እንደማይኖር ህወሀትም ሆነ ደጋፊዎቹ ሊያውቁት የሚገባ ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ መድረሱን ወጣቱ ትውልድ ማሳየት ይኖርበታል።

በመሆኑም ቄሮም ሆንክ ፋኖ፣ ዙርማም ሆንክ ነብሮ ከእንግዲህ በያዝከው አቋም እስከመጨረሻው ድረስ እንደ ሄንሪ ፓትሪክ ነጻነቴን ስጠኝ አሊያ ደግሞ ሞቴን ወዲህ በል ብለህ ግፋበት። ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልህም፣ መቼም የማይተኩ ብቅርቅዬ ወንድሞችህንና እህቶችህን በወያኔ ጨካኞች ጥይት ብታጣቸውም፣ እናትና አባቶችህ ቢዋረዱም፣ ታሪክህ፣ ባህልህ፣ ኢትዮጲያዊነትህ የዘረኞቹ የህወሃት/ወያኔዎች መሳቂያና መሳለቂያ ቢሆንም፣ ከዚህ ሁሉ  የጨለማና የስቃይ ዘመን ባሻገር ብርሃኑ በቅርብ ርቀት እየታየ ነው። የዲሞክራሲ ብርሃን፣ የአንድነት ብርሃን፣ የእኩልነት ብርሃን ፡ የኢትዮጲያን ትንሳኤ የሚያመላክት ብርሃን። ወደዚህ ብርሃን የሚወስደው መንገድ ደግሞ ሌላ ሳይሆን ነጻነቴን ስጠኝ አሊያ  ደግሞ ሞቴን ወዲህ በል! ብቻ ነው።