አምንስቲ ኢንተርናሽናል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በፅኑ እንደሚቃወም ገለፀ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም ያፀደቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት እንዲቀጥል የድጋፍ ድምፅ መስጠቱን ተከትሎ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ተቋውሞውን ገለጸ።

የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዳፀደቀው ከተዘገበ ከሰዓታት በኋላ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ በውሳኔው ቅር መሰኘቱን ገልጿል። በገዢው ፓርቲ እና በእህት ድርጅቶቹ አባላት የተጠቀጠቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲፀድቅ ድጋፍ መስጠቱ ኃላፊነት የጎደለው በማለት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ፀሐፊ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የህዝቡን መሰረታዊ የነፃነት ጥያቄዎችን ማዳመጥ በሚገባበት ወቅት ነፃነትን የሚነግፍ እንዲህ አይነቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማፅደቁ ተስፋ አስቆራጭ ነው በማለት ፀሐፊው አዋጁን ኮንነዋል።

የፖለቲካ ትኩሳቱ እንዲህ በጋለበት እንዲሁም ተቃውሞ በተስፋፋበት ወቅት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የበለጠ የሰብዓዊ መብት መከበር እንጂ በተቃራኒው እንዳልሆነ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ፀሐፊ ገልጸዋል።

ፀሐፊው፣ ከዚህ በፊት የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካታ የመብት ረገጣዎች፣ ያለአግባብ እስራቶች፣ ግድያዎች የመሳሰሉት አለም አቀፍ የሰው ልጅ መብትን የሚጣረሱ ድርጊቶች ሲከናወኑ እንደነበረ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሲያጋልጥ እንደቆየ  በአዲሱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ አክለው አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የሕዝቡን ዲሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ማስተናገድ ተስኖት በሶስት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳይፀድቅ የሚያሳስብ መልዕክት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በየካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም  ለፓርላማ ተወካዮች እንደላከ አስታውቋል።