አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ይፋ ያደረጉት ቁጥር ስህተት እንደሆነ ኢቢሲ ገለፀ

አባይ ሚዲያ ዜና

የህገ መንግስቱን ስርዓት ለመጠበቅ በሚል ሰበብ የህዝብን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የካቲት 9, 2010 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3 ኛ ድምፅ እንዳፀደቀው ገልጿል።

አጠቃላይ የምክር ቤቱ አባል 539 ሲሆን በዛሬው ስብሰባ የተገኙት 441 ናቸው። አዋጁ እንዲፀድቅ ድጋፍ የሰጡ 346፣  88ቱ ደግሞ ሲቃወሙት ሌሎች 7 አባላት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።

አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በምክር ቤቱ ከተገኙ አባላት  346ቱ ድጋፍ መስጠታቸውን በመግለፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለቀጣዩ ስድስት ወራት ተግባራዊ እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ መፅደቁን ይፋ አድርገዋል። 

የመንግስት  ቴሌቭዥን ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አመሻሹ ላይ ያስተላለፈው ዜና በተቃራኒው አፈ ጉባኤ አባዱላ የሰጡት ቁጥር ስህተት እንደሆነ በማሳየት የድጋፍ ድምፅ የሰጡት 346 ሳይሆኑ 395 እንደሆኑ ተዘግቧል።

የተለያዩ የዜና አውታሮች በፓርላማው ውስጥ ሆነው የድምፅ አሰጣጡን ሲከታተሉት እንደነበረ የተገፀ ሲሆን፤ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ 346 ድጋፍ ተገኝቷል ብለው በይፋ ተናግረው ፓርላማውን ከበተኑ በኋላ በመንግስት ሚዲያ 49 ተጨምሮ ድጋፍ የሰጡ 395 እንዲሆን ተስተካክሎ መቅረቡ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ዘገባ መሆኑ ትችት ከተለያዩ አቅጣጫዎች እያስተናገደ ይገኛል።

አዋጁን የተቃወሙት የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ተወካዮች መሆናቸው እየተነገረ ሲገኝ፤ ይህን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ  በፓርላማው ውስጥ የተፈጠረው ክስተት ባለፉት 26 ዓመታት ሆኖ የማያውቅ እንደሆነ እና በኢህአዴግ እህት  ድርጅቶች ውስጥ ያለውን አለመግባባትና መከፋፈል በግልፅ የታየበት እንደነበረ ተነግሯል።

ኢህአዴግ በበላይነት በሚመራው መንግስት እና ፓርላማ ውስጥ አንድን አዋጅ ላለማፅደቅ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፅ ሲመዘገብ ይሄኛው የመጀመሪያ እንደሆነ ተንታኞች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች አስተያየታቸውን እያሰፈሩ ይገኛሉ።

የአገዛዙ ደጋፊ እንደሆኑ የሚታወቁት ምዕራብያውያን እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲቃወሙ እንደቆዩ መዘገቡ ይታወሳል።