ሱዳን አምባሳደሯን ዳግም ወደ ግብፅ እንደምትልክ አሳወቀች

አባይ ሚዲያ ዜና 

የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ሻክሮ በመካከላቸው ቅራኔ በግልፅ ሲያስተናግዱ የቆዩት ሱዳን እና ግብፅ ልዩነታቸውን በማጥበብ ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ።

በሱዳን እና በቱርክ መንግስታት እየተጠናከረ የመጣው የወታደራዊ ግንኙነት ለአገሬ ስጋት ፈጥሮብኛል በሚል ምክንያት ግብፅ ከሱዳን ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል።

በግብፅ የሚገኙትን አማሳደሯን ከካይሮ ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ በመስጠት የሁለቱን አገር ዲፕሎማሳዊ ግንኙነቱን እስከማቋረጥ የሚደርስ ውሳኔ በሱዳን በኩልም ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ መደረሱ ይታወቃል።

የሱዳን እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በሁለቱ አገራት መካከል ጤናማ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም እንዲያብብ የተለያዩ ውይይቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም መሰረት በሚቀጥለው ሳምንት ሱዳን አምባሳደሯን ዳግም ወደ ግብፅ እንደምትልክ ተዘግቧል።

በሁለቱ አገራት እና ህዝቦች መካከል ታሪካዊ የሆነ ግንኙነት እንዳለ በመጥቀስ ይህንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ጠብቆ ማቆየት ሃላፊነት የሚጠይቅ እንደሆነ የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተናግረዋል።

ሱዳን በአከባቢው የቱርክ ወታደሮችን እንዲሰፍሩ ማድረጓን ግብፅ በመቃወም ክሷን ስታሰማ፣ ሱዳን በተራዋ በአገሯ ፖለቲካ ውስጥ ግብጽ ጣልቃ እየገባች እንደሆነ በመጥቀስ ክሷን ስታቀርብ ቆይታለች።

ከካይሮ ጋር በነበረው የሻከረ ግንኙነት ምክንያት ከግብፅ ወደ ሱዳን የሚገቡ የእርሻ ምርቶች ላይ የሱዳን መንግስት እገዳ ጥሎ እንደነበር ይታወቃል።