የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያወጣው መግለጫ አሳፋሪ እንደሆነ የህብረቱ የፓርላማ አባል ገለጹ

አባይ ሚዲያ ዜና 

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠጠር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ገለጹ።

ፖርቹጋላዊዋ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ወ/ሮ አና ጎሜዝ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ እና የመብት ረገጣ አስመልክቶ የአውሮፓ ህብረት ያወጣው መግለጫ ጠጣር ያልሆነ በማለት መግለጫውን ኮንነዋል።

በኢትዮጵያ በሶስት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት የሰጠው መግለጫ ከዩናይትድ ስቴትስ መንግስት መግለጫ ጋር ሲነፃፀር በጣም ደካማ እንደሆነ የህብረቱ ፓርላማ አባል ትችታቸውን አስፍረዋል።

የአውሮፓ ህብረት በመላ ኢትዮጵያ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አገዛዙ በገጠመው የህዝብ ተቃውሞ እንዲሁም የውስጥ ሽኩቻ ዙሪያ የሰጠው መግለጫ በጣም አሳፋሪ በማለት የፓርላማ ተወካይ  የሆኑት ወ/ሮ አና ጎሜዝ ተቃውሞዋቸውን ገልፀዋል።

የአውሮፓ ህብረት የጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣናቸው የመልቀቅ ጥያቄን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስመልከት ያወጣው መግለጫ አገዛዙ ለሁለተኛ ጊዜ የደነገገው የአስቸኳይ አዋጅ የዜጎችን መብት መንፈግ እንደሌለበት የሚገልጽ ይዘት ያዘለ የተለሳለሰ እንደሆነ ይታወሳል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በበኩሉ ህዝቡ እያነሳ ያለው የፖለቲካ፣ የመብት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደማይፈቱ በመግለፅ ከአውሮፓ ህብረት መግለጫ በጠጠረ ይዘት አዋጁ ላይ እንደማይስማማ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል።