የመንግስት የመከላከያ ሰራዊት በአምቦ ነዋሪዎችን መግደላቸው እና ማቁሰላቸው ተሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚያጨቃጭቅ ሁኔታ እንደፀደቀ ከተነገረ  በኋላ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተቃውሞ እና የህዝብ አመጽ ማገርሸቱ እየተነገረ ይገኛል። 

የስራ ማቆም አድማ በአምቦ ከተማ መጠራቱን ተከትሎ የመንግስት የመከላከያ ሰራዊት ከህዝቡ ጋር እንደተጋጩ የሚወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። ከአምቦ በተጨማሪ አዋጁን በመቃወም በወለጋ የህዝብ እምቢተኝነት እየተስተዋለ እንደሆነ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እየተጣሰ እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል።

በአምቦ የመንግስት የመከላከያ ሰራዊት በህዝቡ ላይ በወሰዱት እርምጃ ህይወታቸው ያለፈ ነዋሪዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ወደ አምቦ በተሽከርካሪ የገቡ የመንግስት ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ ይህ ዜና እስከ ተጠናከረበት ሰአት በትንሹ 4 ነዋሪዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ተሰምቷል።

የክልሉ ፖሊስ አባላት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ያለመግባባት ችግር ውስጥ እንደነበሩ ሲነገር፣ በችግሩ አንድ የክልሉ ፖሊስ አባል ሲጎዳ ሌላው ህይወቱ እንዳለፈም ተሰምቷል።

በመከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ የተጎዱ በርካታ ነዋሪዎች ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና ህክምና እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በሁኔታው ቁጣው የገነፈለው ነዋሪ በመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪ ላይ እርምጃ በመውሰድ በእሳት ነዶ ከጥቅም ውጭ እንደሆነም ተነግሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን እንዲያፀድቅ በተደረገው የድምጽ ቆጠራ በሚያምታታ እና በተጭበረበረ መንገድ አዋጁን እንዲፀና መደረጉ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱ ይታወሳል።