አባዱላ ገመዳ ስህተቱ የኔ የነው በማለት ይቅርታ ጠየቁ

አባይ ሚዲያ ዜና

በሁለት ሶስተኛ የድጋፍ ድምጽ ጸድቋል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአደማመር ስህተት እንደነበረበት የህዝብ ተወካይ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ገለጹ።

አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በሶስት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መንግስት የደነገገውን የአስቸኳይ አዋጅ ለማጽደቅ የፓርላማ አባላት በሰጡት ድምጽ ቆጠራ ላይ የተፈጸመው የሂሳብ ስህተት የእሳቸው ድክመት እንደሆነ በማሳወቅ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የደገፉት፣ የተቃወሙት እና ድምጸ ተአቅቦ የሰጡትን የፓርላማ አባላት ቁጥር ሲደምሩ ስህተት እንደፈጸሙ የተናገሩት አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ አዋጁ 346 የድጋፍ ድምጽ ማግኘቱን በፓርላማ ውስጥ ሲናገሩ የሚያሳይ የምስል እና የድምጽ ቪዲዮ እንደ መረጃ መቅረቡ ይታወሳል። 

አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ እንዲሁም በመንግስት የሚተዳደረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአሁኑ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ አዋጁን የደገፉት 395 የፓርላማ አባላት እንደሆኑ ሲገልጹ፣ የመንግስት ደጋፊ እንደሆነ የሚነገርለት የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዋጁ እንዲጸድቅ ድጋፍ የሰጡት 390 የፓርላማ አባላት ናቸው በማለት አምስት ቁጥሮችን ቀንሶ ለአንባቢያን አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡ ማግስት በሚንስትሮች ምክር ቤት የቀረበውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተካሄደው ሂደት መሰረታዊ የሂሳብ እውቀት ማነስ የታየበት ከመሆኑም በላይ የማይጭበርበር ሁኔታም የተስተዋለበት እንደነበረ አስተያየቶች ያመለክታሉ።