ቁርፂ እወ ቁርፂ! (በድንበሩ ደግነቱ)

0

እውነት መሆናቸው ያልተረጋገጡ ነገሮች ደጋግመው በተነገሩ ቁጥር በሰፊው ተቀባይነት እያገኙ ለማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ ላይ ይደረሳል። ይህን ያሰኘኝ በተደጋጋሚ ህወሀትን እየደገፉ በየመገናኛ ብዙሐን ብቅ እያሉ የሚሙዋገቱ፥ በአብዛኛው ከትግርኛ ተናጋሪው ወገናችን የበቀሉ ኢትዮጵያውያን፥ “የትግራይ ሕዝብ ደርግን ታግሎ ጣለ!” የሚለውን ሙግት ሁልጊዜም በክርክራቸው ወቅት እንደ ጠጣር እውነት ይጠቅሱታል። በተቃራኒው ወገን ሆነው የወቅቱን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት እንቅስቃሴን ደግፈው የሚሙዋገቱ  ወገኖችም ይህን ብሂል እንደ እውነት ተቀብለው ነው ክርክሩን የሚገፉበት። እውነት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ የተገንጣዮችን አላማ ደግፎ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አንፃር ቆሞ አምኖበትና ፈቅዶ ተዋግቶዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ እርግጠኛ መልስ የሚያገኘው ሕዝቡ ያለፍርሀት ድምፁን የሚሠጥበት ሁኔታ ተመቻችቶለት፥ እውነተኛ ድምፅን ቆጥሮ የሚያረጋግጥ አካል ተፈጥሮ በተረጋገጠ የውሳኔ ሕዝብ ብቻ ነው። እንኩዋን የሚሊዮኖችን ድምፅ፥ በርካታ መገናኛ ብዙሐን የታዘቡትን የ539 የፓርላማ አባላትን ውሳኔ የዘረፈ ወንበዴ ሥልጣን ላይ ሆኖ፥ ይህ ይሆናል ማለት ዘበት ነው። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ የቀድሞውን ሠራዊት ተዋግቶዋል የሚለው ሃሳብ ግምት ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይህም “ግዙፍ ሠራዊት የነበረው የቀድሞው ጦር የትግራይ ሕዝብ ባይዋጋው ኖሮ እንዴት በህወሀት ብቻ ይሸነፋል?” በሚል እሳቤ የትግራይን ሕዝብ ከህወሀት ጋር ለማዳበልና፥ ህወሀት በኢትዮጵያውያን ላይ ለሚያደርገው ግፍ የትግራይን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ የሚያደርገው ጥረት ነው። ለዚህም የትግራይ ተወላጅ ምሁራን ዐይናቸውን በጨው አጥበው ይሙዋገቱለታል።

እርግጥ ጦርነቱ “የኔ አንገት ይቆረጣል እንጂ አገሬ አትቆረስም!” ይል በነበረው የቀድሞ ጦርና፥ “ትግራይንና ኤርትራን ገንጥለን እንወስዳለን!” ይሉ በነበሩ በቀድሞው መንግሥት አጠራር “የናት ጡት ነካሾች!” መካከል ነበር። በቀድሞው መንግሥት በኩል የግለስቦችን የሥልጣን ጥም ለማርካት ሲባል በገዛ ወገኑ ላይ በፈፀመው በደል ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኩዋን ከጎኑ አልቆመም ነበር። በሶሺያሊስት ፍልስፍና ተተብትቦ፥ ጦሩ በጄኔራሎቹ ዕውቀት ሳይሆን በካድሬዎቹ ይመራ ነበር። ከግንቦት ስምንቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በሁዋላ፥ አገሪቱ ትመካባቸው የነበሩትን ጄኔራሎች ወንበዴዎቹ ሳይሆን ራሥ ወዳድ የአገሪቱ መሪ ነው ያስወገደላቸው። በተለይ ከሶቭየት ህብረት መበተን በሁዋላ የቀድሞው መንግሥት ብቻውን የቀረ ሲሆን፥ ጠላቶቹ ግን ደጋፊዎቻቸው የትየለሌ ነበሩ። ሻዕቢያና ወያኔ አንድ ላይ፥ የአረብ አገሮች  በአብዛኛው፥ የሱዳን መንግሥት መቶ በመቶ፥ የአሜሪካን መንግሥትና CIA አንድ ላይ ሆነው ነበር የኢትዮጵያን ጦር የገጠሙት። ስለዚህ ውጊያው በዓለም ኃያላንና፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኩዋን ድጋፉን ከነፈገው ከቀድሞው መንግሥት ጋር ነበር። የዛ ጦር መሸነፍ በምንም ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ ትግራይን መገንጠል ዓቢይ ዓላማ ያደርጉ የነበሩትን የናት ጡት ነካሾች ደግፎ ተዋግቶዋል ከሚለው መደምደሚያ ሊያደርስ አይችልም። ይህ ተረት ኃላፊነት የጎደለው ሠፊውን የትግራይ ሕዝብ የሚያጠለሽና በታሪክም ተወቃሽ የሚያደርገው ውሸት ነው። የትግራይ ሕዝብ ትግራይን ለመገንጠል አልተዋጋም። ወያኔ የተዋጋው ትግራይን ገንጥሎ ሥልጣን ለመጎናፀፍና ለመዝረፍ ነበር። ይህም ተሳክቶለታል።

ወያኔ ከጅምሩ “አላማችሁ ትክክል አይደለም!” ያሉትን “ትግራይ የኢትዮጵያ እንብርት እንጂ ራስዋን የቻለች አገር አይደለችም! ከአማራ ጋር የተዋለድን ወንድማማች እንጂ ጠላት አይደለንም!” ያሉትን የትግራይ አዛውንቶች ከየቤታቸው ለቅሞ ያደረሠበት አይታወቅም። ጥፋት የጀመረው የራሱን አባቶች በመግደል ነው። የትግራይ ሕዝብ በረሀብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ፥ ደርግ እንኩዋን ባረፈበት ዓለም አቀፍ ግፊት፥ ረሀቡን ለመከላከል ደፋ ቀና ሲል፥ ህወሀት በሚሊዮን በሚቆጠሩት  ትግራዋይ ወገኖቻችን እልቂት የኤኮኖሚ  የፖለቲካና የጦር ሜዳ ጠቀሜታዎችን (advantage) አካብቶዋል። በሸፍጥ ለደርግ ባለሥልጣኖች በላከው አሳሳች መረጃ፥ በገበያ ላይ የተሰጣን ገበያተኛ በቦንብ አስደብድቦ የከሰለ የወገኖቻችንን ሰውነት በቪድዮ ቀርፆ የድል ጎዳናውን ጠርጎበታል።

ህወሀት መቀሌን ሲቆጣጠር ትግራይን ጥለውለት አገራችን ወደአሉዋት ወደ ተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ትግራዋያን ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ኢትዮጵያም ልጄ ብላቸው እኛም ወንድምና እህቶቻችን በመሆናቸው በችግርም ውስጥ ሆነን ተቀብለን በጠባብዋ ቤታችን ጠጋ ጠጋ  ብለን አስተናግደናቸው ነበር። አዎ “ቁርፂ እወ ቁርፂ” ብለን አብረን አዚመን ነበር። እነሱም የትግራይ ሕዝብ ናቸው። ታፍኖ ያለውን ሕዝብ የህወሀት ደጋፊ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ የጥቂት ምሁራን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። ህወሀት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ነው። የትግራይ ሕዝብ ታፍኖ ነው እንጂ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች ጋር አይወግንም።

ድጋሚ ጥሪ ለትግራይ ምሁራን!
ኢትዮጵያዊ የተነሳው ከጥግ ጥግ ነውና የልቡ ሳይደርስ የሚያቆመው ምድራዊ ኃይል አይኖርም። የትግራይ ምሁራን በየዜና ማሰራጫው እየቀረቡ ህወሀትን ለማትረፍ ከሚታትሩ፥ ከተቀረው ወንድማቸው ጎን ቢሰለፉ አባጣ ጎርበጥባጣውን መንገድ የጨርቅ ባደረጉት ነበር። ህወሀት የተጣላው ከኦነግ፥ ወይ ከግንቦት ሰባት፥ ወይም ከሠማያዊ ፓርቲ አይደለም። ህወሀት የተጣላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው። የገባንበት ገደል ደቡብ አፍሪካውያን በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከነበሩበት ማጥ ጋር ይመሳሰላል። የNational Party ዴክለርክን የመሰለ አስተዋይ ሰው ነበረው። ህወሀት እንዲህ አይነት አርቆ አሳቢ የለውም። ለጥያቄዎች ሁሉ መልሱ ቆረጣና ጥይት ነው። ችግሩ ጥይት የማይፈራ ትውልድ ተፈጥሮዋል። ሲሆን ወንድሞቻችሁ ነንና ወጥታችሁ ተቀላቀሉን። ያም ቢቀር ውስጥ ውስጡን የትግራይ ሕዝብን በማረጋጋት፥ ትግሉ ለትግራይ ሕዝብም ነፃነት መሆኑን ስበኩ። ያም ካልሆነ ህወሀትን አኩርፉት። በየመገናኛ ብዙሐን እየቀረባችሁ፥ የግፉአንን የነፃነት ትግል ጥላሸት አትቀቡ። እነዚህ ወጣቶች ርሃብ፥ እርዛት፥ ሥራ አጥነት፥ እሥር፥ ግርፋት፥ ግድያ ያስመረራቸው ናቸው። ለህወሀት አገራቸውን ጥለውለት ወንድሞቻቸውን ለሻርክ መንጋጋና ለአይሲስ ካራ እየዳረጉ ተሠደው ነበር። የሰው አገር የሰው ነውና ማጅራታቸው እየታነቀ ወደ አገራቸው ተመለሱ።

የደላቸውና ጠግበው የደፉት ምግብ የቆሻሻ ገንዳውን በሚሞላበት ባደጉት አገሮች፥ አመጽ በተነሳ ቁጥር ሱቆች ተሰብረው ሲዘረፉ አይታችሁዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ባለው ንቅናቄ፥ ቢዘርፉ የህወሀት ዘረፋ ለመራባቸው ቀጥተኛ ምክንያት የሆነባቸው ስንትና ስንት ወጣቶች ወስፋታቸውን ደፍነው ባደሩ ነበር። ወጣቶቹ አርቀው የሚያስቡ ናችው። ይህ አላታለላቸውም። ህወሀት በወታደራዊው ቁንጮ በኩል “ህወሀትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው” ሲል እናንተ ዝም በማለታችሁ ከመታዘብ በቀር አላመኑትም። ቄሮና ፋኖ እጅግ ጥንቃቄ (surgical precision) በተመላበት ሁኔታ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በሀሰት መኮነን አቁሙ። አንደኛ ህወሀትን የደገፉ ትግሬ ያልሆኑ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሁለተኛ ትግሬ ሆነውም ጥቃቱ በአጠገባቸውም ያላለፈ ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። የወጣቶቹ ብስለት ሆኖ ነው እንጂ፥ የመከላከያ ጄነራሎች ከመቶው ዘጠና ስምንቱ ትግሬ መሆናቸውን ዘንግተውት አይደለም። ሕፃን፥ ሴት፥ ሽማግሌ ሳይመርጥ ትግሬ ያልሆነውን ሁሉ ያለርህራሄ የሚገድለው አግአዚ፥ ከትግራይ የተውጣጣ መሆኑን አልሳቱትም። ጉራጌ ከመርካቶ ጥርግ ተደርጎ ወጥቶ በህወሀት ደጋፊ ትግሬ መተካቱን አይተው አልፈውታል። የነሱ ፊት ድሥት ከተጣደበት ወራት እንደሆነው ምድጃቸው አመድ ሲነፋበት፥ ትግሬ የሆኑት ጎረቤታቸው ፊታቸው ከቀን ወደ ቀን ወዝ ሲተፋ አይተው ንቀውታል። ይህን ሁሉ ያደረጉት ትግሬ ማለት ህወሀት አይደለም፤ የትግራይ ሕዝብ ወንድማችን ነው ብለው ስላመኑ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ወጣቶች ነገን ማበላሸት የማይፈልጉ ተሥፋን የሠነቁ ናቸው። የተፈጥሮ ኡደታቸውን ጨርሰው ልጣቸው ርሶ ከመቀበሪያቸው ጉድጏድ አፍ ላይ ከተቀመጡና እኔ ከሞትኩ በሚል ፍልሥፍና የትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂትን ለመጋበዝ ከቆረጡ አዛውንቶች ጋር አትቁሙ። ከእነዚህ ወጣቶች ጎን ብትቆሙ ባዶ ሥድሥትን ከፍተው የጠፉባችሁን ወገኖች እንድታገኙ ይረዱዋችሁዋል።

አብረን እንደገና “ቁርፂ እወ ቁርፂ” እንዘምር!!