የስራ ማቆም አድማው ትራንስፖርት እና ንግድን አስተጓጉሏል

አባይ ሚዲያ ዜና 

መንግስትን በመቃወም የተጠራው የስራ ማቆም እና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተጀምሯል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሚያሻማ እና ግልጽ ባልሆነ የድምጽ ቆጠራ ጸድቋል መባሉ የህዝቡን ቁጣ ዳግም አገንፍሎ የስራ ማቆም አድማ ጥሪ እዲደረግ ምክንያት ሆኗል። በአድማው ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተስተጓጎለ የወጡት መረጃዎች ሲያሳዩ በአዲስ አበባ አውቶቡስ ተራ ከወትሮው በተለየ መልኩ የህዝብ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ቁጥራቸው እንደቀነሰ ለመረዳት ተችሏል።

በለገጣፎ ነዋሪዎች የንግድ ሱቆችን በመዝጋት የህዝብ እምቢተኝነቱን እና በአገዛዙ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በቤት ውስጥ በመቀመጥ አድማ እየገለጹ ይገኛሉ።

በወልቂጤ ከተማ አገዛዙን በመቃወም የስራ ማቆም አድማውን ለማስቆም ጥረት አላደረጋችሁም በሚል ውንጀላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ባለስልጣናትም እንዳሉ ከቦታው የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከማስነሳት በተጨማሪ የስርአት ለውጥን ያነገበው የህዝቡ እምቢተኝነት እና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ በሰበታ፣ በአለም ገና፣ በቡራዩ፣ በአምቦ እንዲሁም በምእራብ ሐረርጌ መቀጠሉን ለመረዳት ተችሏል።