የዩናይትድ ስቴትስ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሊወያዩ እንደሆነ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና የዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸው በኢትዮጵያ ተገናኝተው ውይይት ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ተገለጸ።

የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ተገኝተው ውይይት እንዲያደርጉ ከሩሲያ በኩል የቀረበ ሃሳብ እንደሆነም ተዘግቧል። ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢትዮጵያ ውስጥ ውይይት ለማድረግ ሞስኮ ጥሪ እንዳቀረበች ታውቋል።

የሶሪያ ወቅታዊ የፖለቲካ እና የጸጥታ ጉዳይ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ዋና አጀንዳ እንደሚሆን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ከሩሲያ እና ከዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተጨማሪ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርም በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው አገዛዙን በመቃወም እየተቀጣጠለ ስለመጣው የህዝብ እምቢተኛነትና መንግስት እየወሰደ ስላለው የሃይል እርምጃ ዙሪያ ላይ እንደሚመክሩ ተነግሯል።

በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ቀውስ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ በተቃወመችው እና አጨቃጫቂነቱ እየጨመረ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዙሪያ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን ይመክራሉ ተብሏል። 

ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡት ከጠቅላይ ሚንስትር ሃይለ ማርያም ጋር እና  ከሌሎች የአገዛዙ ባለስልጣናት ጋር የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እንደሚወያዩ የወጡት መረጃዎች ያመለክታሉ።

.