የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገለጹ

አባይ ሚዲያ ዜና 

በአፍሪካ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኢትዮጵያ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄው የበለጠ ነፃነት መስጠት እንደሆነ ተናገሩ።

የፖለቲካ ትኩሳቱን ለማብረድ የሚያስፈልገው ነጻነትን መገደብ ሳይሆን የበለጠ ነጻነትን መስጠት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን በመጠቆም አጨቃጫቂውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም  ተችተዋል።

መንግስት በተለያዩ ቦታዎች የተነሳውን የህዝብ ቁጣ እና አመጽ ለመቆጣጠር እያደረኩ ነው በማለት የሰጠውን ገለጻም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በማወደስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውሞዋን አሁንም እንደምትገልጽ አሳውቀዋል። በኢትዮጵያ እንዲመጣ ለሚፈለገው የፖለቲካ መረጋጋት መንግስት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቀልበስ እንዳለበት ቴለርሰን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሶስተኛ አመት ያስቆጠረውን የህዝብ ተቃውሞ እና ቁጣ የሚመሩት መንግስት በሰላም መፍታት ስለተሳነው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል ሰበብ ስልጣናቸው በፍቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የጠቅላይ ሚንስትሩን ስልጣን ለመያዝ የሚደረገው የስልጣን ሽግግር ሂደቱን በመደገፍ እንዲህ አይነቱ የስልጣን ርክክብ የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ መጎልበት ያሳያል ብለዋል።

ከህዝብ እምቢተኝነቱ በተጨማሪ በውስጥ ሽኩቻ እየታመሰ ያለው የኢህአዴግ ድርጅት በመጪው እሁድ ስብሰባ ለማካሄድ መርሃ ግብር ማውጣቱን ማሳወቁ ይታወሳል። በኢህአዴግ ውስጥ ከሚገኙት እህት ድርጅቶች መካከል ኦህዴድ ህወሃትን በግልጽ እየተገዳደረው በመምጣቱ የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን ወደ ኦህዴድ ሊሄድ ይችላል የሚል ከፍተኛ ግምት እየተሰጠው ይገኛል።

ከመብረድ ይልቅ እየተቀጣጠለ ያለው የህዝብ እምቢተኝነት እና ተቃውሞ ህይወት እያጠፋ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ መንግስትንም እያሳሰበው እንደሆነ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ችግሩን ለመፍታት የህዝብን ነጻነት መገደቡ ትክክል እንዳልሆነ ቴለርሰን ገልጸዋል።