ኃይሌ ገ/ሥና ምሩፅ ይፍጠር፣ የዘር ፖለቲካ ወላፈንዲ! (በድንበሩ ደግነቱ)

0

ኃይሌ በሄድክበት ሁሉ ባንዲራችን ስለተውለበለበ እንደ ባንዲራችን ከፍ አድርገን ተሸክመንህ ቆይተናል። ባንዲራችን ነፃናታችን ስለሆነና እኛም ነፃነታችንን ስለምንወድ በተደጋጋሚ ስታላግጥብን ችለንህ ነበር። አሁን ግን ታከተን! ነፃነታችን ማለት ሰው መሆናችን ነው። በመቶ ሚሊዮን ሰዎች ሰውነት ላይ ነው ባልተገራ አንደበትህ በመገናኛ ብዙኃን እየወጣህ የምታላግጠው። ምሥኪን አበበ ቢቂላ ከሾህ የሚከላከል ሁነኛ መጫሚያ በሌላቸው እግሮቹ ሠርቶ  ያወረሰህን ታሪክ አዋርደሀል።  ኃይሌ “ኢትዮጵያን አደራ!” ያለህን ጀግናው ምሩፅ ይፍጠርን ደጋግመህ ገለኸዋል። ምሩፅ ይፍጠርን እግር የሰጠው አምላክ ልብ አልነሳውም ነበርና በሕይወቱ ለሕዝብ እንዳለቀሰ እንጂ፥ እንዳንተ በቁስሉ ስንጥር አልሰደደበትደም። ምሩፅ ይፍጠር ነፍሱን አምላክ በገነት ያኑርልን! ምሩፅ ኃይሌን ግን እዛ አትጠብቀው! የኢትዮጵያ ሕዝብ አልቅሶበታል፥ በወኅኒ እየማቀቁ ያሉት የዋልድባ መነኮሳት አዝነውበታል። ታደሉ ተማም ተው የወለደ ግፍ አይናገርም እያለችው ለሁለት ሴት ልጆቹ ሳይራራ የግፍ መዓት ይተፋል።

ኃይሌ የወቅቱ የዘር ፖለቲካ ካንተ ይልቅ ለምሩፅ የሀብቱን ቁልቁለት ዝቅ ያደርግለት ነበር፤ ምን ያደርጋል ምሩፅ አምላክ ካንተ ወስዶ ልቡንና አዕምሮውን ጨመረለትና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያለቅስ ሕይወቱ አለፈ። አሁን በገነት ከአቡነ ጴጥሮስ ጎን ተቀምጦ ኃይሌስ እንዴት ነው ብለው ሲጠይቁትና ምሩፅም የሚለው ጠፍቶት ሲሸማቀቅ ይታየኛል። የዘር ፖለቲከኞች የዘር ፖለቲካ ቀሺም መመዘኛ እንደሆነ ምሩፅ ይፍጠርና ኃይሌ ምሥክር ናቸው። በእርግጥ ምሩፅ ይፍጠር ኃይሌን አስተካክሎ አለመፍጥሩ ሊያስወቅሰው ይችላል። በሮጠለትና ባስከበረው ባንዲራ እንደኮራ ተሰናብቶዋል። እንደኃይሌ አንገት አላስደፋንም። ኃይሌ ያደረግህብን ካደረግህልን በብዙ መቶ አጠፈ። ላደረግኸው ተገቢውን የሕዝብ ከበሬታ ተለግሶሀል። ከተገቢውም በላይ ሀብት አካብተሀል። ምሩፅ ይፍጠርና አበበ ቢቂላ ድሀ ሆነው ነው የሞቱት። የሕዝብ ፍቅርና የታሪክ ሀብት ግን ሞልቶ ፈሶዋቸዋል። አንተ በአዲስ አበባ ቦሌ ሃምሣ ሜትር ከመሬት በታች ቆፍረህ ሕንፃ ተክለሀል። ምሩፅ ይፍጠር በልባችን ውስጥ ክብርን፥ ፍቅርንና ዕዳን ተክሎብን አልፎዋል። አንተ ወደፊት ለልጆችህ አባታችሁ እኮ እያሉ ወራዳ ንግግርህን እያበጠሩ የሚተርኩ ሰዎችን እንጂ መልካም ሥምህን እያወረስካቸው አይደለም። ግን ኃይሌ ኢትዮጵያና ሕዝብዋ ምን በደሉህ? አንድ ሁለት ብዬ ልቁጠርልህ አጥብቀህ ትንቃቸዋለህ፥ ትጠላቸዋለህ።

  1. መሀል ኢትዮጵያ ውስጥ እያደጉ ልጆችህ ኢትዮጵያዊ ቁዋንቁዋን እንዳይናገሩ ከልክለሀቸዋል።
  2. ኢትዮጵያና ሕዝብዋ ለነፃነታቸው “ሆ!” ብለው በተነሱበት የ97 ምርጫ ወቅት አብረሀቸው በመቆም ፈንታ፥ ነጭ ፀጉራቸውና ዘወትር የሚለብሱት የኩሩው ሕዝብ ሸማ ኅሊናቸውን ካልቆጠቆጣቸው አዛውንት ጋር ተሰልፈህ መሪዎቻችንን “የሚያዋርድ” የመለስ ዜናውን ፖለቲካ የሚጠግን ተልዕኮ አሳካህ።
  3. የእናት ጡት ነካሹ መለስ እውነተኛ ገመና ለዓለም በተጋለጠበት ወቅት አንተ ማልያህን፥ ያራም ዶላርን በመሽለም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሌሎች ቀጣይ የባርነት ዘመናት አዘጋጃችሁለት።
  4. አንተና የህወሀት ደጋፊዎች በሀብት ሠገነት ላይ ስለወጣችሁ ብቻ ጦሙን የሚያድረውና መሬቱን የተነጠቀው ህዝብ ሁሉ የለማ ይመስል “የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቡቱቶውና ከአሮጌ ኑሮው መላቀቅ ስለማይፈልግ ልማትን አይደግፍም።” አልክ። ይህን ሀሳብ ሰው የሆነ በተለይም ኢትዮጵያዊ ሊያስበው ይገባል? ቢያስበውስ ሊናገረው ይገባል? – ያውም በአደባባይ!
  5. ተው እንጂ እያሰብክ ተናገር የሚልህ ጠፋና “ዲሞክራሢ ለአፍሪካ ቅንጦት ነው!” ብለህ ዘረኛ ነጮች እንኩዋን የማይናገሩትን ደፋር ውሽት አሁንም በአደባባይ ተናገርክ። ዲሞክራሢ ማለት በጥቅሉ ነፃነት ነው። ነፃነት ደግሞ ስትፈጠር ከፈጣሪህ የምትቀበለው ፀጋ ነው። ይህ ለማንም ተራ ዜጋ ረቂቅ ያልሆነ ሀሳብ ነው። በሆዱ ለሚያስብ ሰው እርግጥ ረቂቅ ሊሆን ይችላል።
  6. ለነፃነታቸው አንድ ያለቻቸውን ነፍስ ሊሰጡለት ቆርጠው አደባባይ ወጥተው አግአዚ እንደአገዳ ለሚቆርጣቸው ወጣቶች እንባህን በማፍሰስ ሐዘንህን መግለጽ ሲገባህ፥ ጭራሽ ትግላቸውን ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ደምረህ አጣጣልክባቸው። ለነገሩ እንባ ከየት ታመጣለህ ለመለስ ስታለቅስ ጨርሰኸዋል። ማወቅ የሚገባህ ግን ብዙ በተናገርክ ቁጥር ከጭካኔህ በተጨማሪ አላዋቂነትህንም እያጋለጥክ ነው። እነማርቲን ሉተር አውቶብስ አንሣፈርም ብለው በማለዳ ተነስተው በእግራቸው የኩዋተኑት ሰላማዊ ትግል በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚያውቁትን ጉዳይ በዓለም ታይቶ የማያውቅ ስትል ዋሸህ። ታዲያ እንዴት ልትከበር ትችላለህ?

ኃይሌ አንተ ላይ ያልደረሱብህ ቅን ነፃነት ናፋቂ ወጣቶችን እያጋለጥህ ለመንግሥት አልሞ ተኩዋሾች አሳልፈህ እየሰጥሀቸው መሆኑ ገብቶሀል? በድፍረት ለጥይት ደረታቸውን የሰጡ ለጋ ሰማዕቶች ደም ላይ እያላገጥክ መሆኑ ገብቶሀል? በዚህ ደማቸው የፈላ ወጣቶች ባንተም ሆነ በንብረትህ ላይ ጥቃት ቢፈጽሙ የመብት ማስከበር ትግል ሆኖ እንደማይቆጠር ከራስህ ወዲያ ማረጋገጫ ማግኘት ሳያስቸግር አይቀርም።

ምነው ጌታ ማስተዋያውን ሰጥቶህ፥ እንደ እባብ እግር በነሳህ ኖሮ! ለኢትዮጵያና ሕዝብዋ የተሻለ በጠቀምክ ነበር።