የአርበኞች ግንቦት 7 ሳምንታዊ ርዕሰ አንቀፅ

እብሪተኛው የህወሃት ከፍተኛ አመራር የአገዛዝ ዘመኑን በጉልበት ለማስቀጠል ያወጣው ሁለተኛ ዙር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ የህዝባችንን የትግል እንቅስቃሴ ለማዳፈን አቅም የፈቀደለትን ሁሉ ግድያ ፤ አፈናና እስር በማካሄድ ላይ ይገኛል። ለህወሃት አፈናና ግድያ አልበገር ያለው ህዝባችን ግን ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከቁብ ባለመቁጠር ለአመታት እየታገለለት ያለውን የዲሞክራሲ ፤ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄውን ገፍቶበታል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ከየካቲት 9 ቀን ወዲህ አዋጁን ለማስተግበር ከተቋቋመው የኮማንድ ፖስት ጋር በመፋጠጥ ህዝባችን እያካሄዳቸው ካሉት ትግሎች መካከል፦

 

  1. አዋጁ በታወጀበት ሳምንት በመካሄድ ላይ የነበረው የጉራጌ ህዝባዊ እምቢተኝነት፣ አዋጁ ከታወጀ በኋላም እስከ የካቲት 15 ቀን ድረስ ለአንድ ሳምንት ዘልቆ የአገዛዙ ቀኝ እጅ በሆኑ የደኢህዴን ካድሬዎችና የዞኑ አስተዳዳሪዎች መኪናዎችና ቢሮዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ በእሳት እንዲጋዩ አድርጓል።

 

  1. የጎንደር ፣ የባህርዳርና አካባቢው ህዝብ አዋጁ ከታወጀ ከ3 ቀናት በኋላ ከየካቲት 12 እስከ የካቲት 14 ቀን ለሶስት ቀናት የዘለቀ የሥራ ማቆም አድማ አድርጎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመብቱ ከመታገል እንደማያስቆመው በተግባር አረጋግጧል።  

 

  1. ላለፉት በርካታ አመታት ለህወሃት አገዛዝ ዋና የህይወት እስትንፋስ ሆነው የኖሩት የህወሃትና አባል ድርጅቶቹ አባላት ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩት የአገሪቱ ፓርላማ ከህዝብ በደረሰበት ግፊት ተከፋፍሎ አዋጁን ለማጽደቅ በህገ መንግሥቱ የሚያስፈልገውን የ2/3ኛ ድምጽ ድጋፍ እንዳያገኝና በድንጋጤ ተውጦ እንደለመደው በአደባባይ  ቁጥር የማጭበርበር ተግባሩ ውስጥ መልሶ እንዲወድቅ በማድረግ አጋልጦአቸዋል። ይህ እርምጃ ህወሃት በጉልበት ህዝባችን ላይ ሊጭነው የፈለገውን አፋኝ አዋጅ ህጋዊነት ያሳጣ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቱ በምዕራባዊያ ወዳጆቹ ዘንድ ሳይቀር እንዲጋለጥና መሳቂያ መሳለቂያ እንዲሆን ያደረገ ነው።

 

  1. የአጋዚን ጭፍጨፋና አፈና ሁሉ ተቋቁሞ ላለፉት 3 አመታት በግንባር ቀደምነት እየተፋለመ ያለው ቄሮ፣ አዋጁ በታወጀ 3ኛ ሳምንት፣ ከየካቲት 26 እስከ የካቲት 28፣ የጠራው ሥራ ማቆም አድማ በአብዛኛው የኦሮሚያ ከተሞች ተካሂዶ ሥርዓቱን ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ የከተተ የጀግንነት ተጋድሎ አስመዝግቦአል ።  

 

  1. በውጪ የሚኖረው ማህበረሰብ የጀመረውን ህወሃትን በኢኮኖሚ የማዳከም ዘመቻው ጎን ለጎን ምዕራባዊያን በህዝባችን ላይ የታወጀውን ይህንን አፋኝ አዋጅ እንዲቃወሙና ለህወሃት ሲያደርጉ የኖሩትን ድጋፍ እንዲያቋርጡ  በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ሰልፎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

ለአብነት የተጠቀሱትን እነዚህን እርምጃዎች በጥቅሉ ብንመረምረው ህወሃት የአገዛዝ ዘመኑን ያራዝምልኛል ብሎ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ያወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸም እንኳ ቢቻል፣ ላለፉት 27 አመታት አገዛዙ ሲፈጽማቸው ከኖረው የጅምላ ጭፍጨፋ እስርና እንግልት የበለጠ የሚያመጣው ምንም አይነት የባሰ መከራና ስቃይ እንደሌለው ህዝባችን ተረድቶ የህዝባዊ ትግሉ ዋና አላማ የሆነውን የነጻነት ትግል ከዳር ለማድረስ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ከወያኔ አገዛዝ ለመላቀቅ መወሰኑን የሚያሳይ ነው። በህወሃት የጦር ጀኔራሎችና የደህንነት ሃላፊዎች የሚመራው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ህዝባችንን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለማስገባት እየወሰደ ባለው እርምጃ ሰሞኑን ለአምቦ ከተማ ቅርበት ባለው ጉደር ከተማ ላይ ነዋሪ የነበሩትን የ65 አመት አዛውንት የ10 ልጆች ወላጅ አባት አቶ ደግፌ የተባሉ ኢትዮጵያዊ መኖሪያ ቤት ድረስ ዘልቆ በመግባት ልጆቻቸውና የረጅም ጊዜ የትዳር ጓደኛቸው ፊት በጥይት ደብድቦ ገድሎቸዋል።  አቶ ደግፌን ለሞት ያበቃቸው ምክንያት ልጃቸውን ለማሠር መኖሪያ ቤታቸው ድረስ የመጣውን የአጋዚ ጦር አባል “ልጄ ምንም ወንጀል አልፈጸመምና አታስረውም” ማለታቸው እንደሆነ ባለቤታቸው ወ/ሮ ቀናቱ ጉርሜሳ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃልመጠይቅ አረጋግጠዋል። ህዝባዊ ተቃውሞው ከጀመረ ወዲህ እንዲህ አይነት የግፍና የጭካኔ እርምጃ በተለያዩ የኦሮሞና የአማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ ተወስዶአል። አላማውም ህዝቡን በፍርሃትና በሽብር አንቀጥቅጦ እስከ ወዲያኛው ተገዢ የማድረግ እሳቤ ነው። ህወሃት ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ እየገዛ ያለው እንዲህ አይነት የጭካኔ እርምጃዎችን በጠራራ ጸሃይ በመውሰድ አገሪቱ ውስጥ የፍርሃት ደመና በማስፈን እንደሆነ ግልጽ ነው። በድህረ ምርጫ  97 አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “ባሌ የሠራው ወንጀል ስለሌለ አትሰሩት” በማለታቸው ልጆቻቸውና ሊከላከሉለት በሞከሩት ባለቤታቸው አይን ፊት በጥይት የተገደሉት ወ/ሮ እቴነሽ ይማም፤ የሰፈር ልጆች በጅምላ መታሰራቸውን አይተው “እባካችሁን ተዋቸው” ለማለት የሞከሩት የ8 ልጆች እናት የነበሩት ወ/ሮ ክብነሽ መርጊያ፤ ሽንኩርት ቸርችረው ያሳደጉዋቸው ሁለት ልጆቻቸውን በአንድ ጀንበር ያጡት የመርካቶ ነዋሪ ሌላኛዋ ወ/ሮ እቴነሽ (የነ ፍቃዱ እናት )፤ የጨርቅ ኳሱን ከምድር አንስቶ ለመሮጥ ጎንበስ ባለበት ተመቶ ህይወቱ የተቀጠፈው የ8 ዓመቱ ታዳጊ ህጻን ነቢዩ አለማየሁ ወዘተ ህወሃት አሁን እየወሰደ እንዳለው ህዝባችንን ፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለመክተትና የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም የወሰደው አረሜኔያዊ እርምጃ ሰለባዎች እንደሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ አልዘነጋም።

ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በአነጣጥሮ ተኳሾች ህይወታቸው ከተቀጠፈ ንጹሃን ዜጎች በተጨማሪ በአገዛዙ ታሪክ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በየክልላቸው ተሰማርተው በማገልገል ላይ ከሚገኙ የፖሊስ፣ የደህንነትና የስቪል አስተዳዳሪዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል አድማ በታኝ ሃይል ዋና አዛዥ የሆነው ኮማንደር ኢያሱ ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አዱኛ ፤ የመቱ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ነገራ ፤ የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጫላ ፤ የምሥራቅ ሃረርጌ ደህንነት ሃላፊ እስክንድር አህመድ ፤ የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ መሰለ ዮሃንስና የዞኑ አስተዳዳሪ እንዲሁም የለገጣፎ ፖሊስ አዛዥና የከተማው አስተዳዳሪ ታግተው እስር ቤት ተወርውረዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች በኦሮሚያ በአማራና በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ከተደረገው ሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ከየቤታቸው እየታደኑ መታሰራቸውም ይታወቃል። ይህ አልበቃ ብሎ ደግሞ ባለፉት ሁለት ሶስት ቀናት ውስጥ በአማራ ክልል ዜጎች እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከጥቃት የሚከላከሉበትን የነፍሰ ወከፍ መሣሪያ የመቀማትና እራሳቸውን የመከላከል አቅም የማሽመድመድ እንቅስቃሴ ተጀምሮአል።

የኢህአደግ ሥራ አስፈጻሚ ከወራት በፊት ባካሄደው ረጅም ስብሰባ አገራችንን ቀውስ ውስጥ ለከተተው የፖለቲካ ችግርና ህዝባችን እያነሳ ላለው የመብት ጥያቄ ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቁ ተዘንግቶና የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት የፖለቲካ ምህዳሩን እናሰፋለን ተብሎ በተወሰደ እርምጃ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እየተጠበቀ ባለበት በዚህን ሰዓት ህወሃት የአፈና እርምጃውን በማን አለብኝነት አጠናክሮ መቀጠሉና የአገሪቱን እሥር ቤቶች እንደገና በእስረኞች ለማጣበብ መወሰኑ ህዝብ በአገዛዙ ላይ ያለውን ተስፋ ያሟጥጣል እንጂ ትግሉን እንደማያቀዘቅዘው ግልጽ ነው።

አርበኞች ግንቦ 7 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ወዲህ ህዝባችን የጀመረው የነጻነት ትግል ከዳር ሳይደርስ በምንም አይነት አፋኝ እርምጃ ሊቆም እንደማይችል በተግባር ላስመሰከሩ የኦሮሚያ፤ የአማራና የወልቂጤ ህዝብ እንዲሁም “ከህዝባቸው ጋር በመወገን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አልተገበራችሁም” ተብለው በኮማንድ ፖስቱ እርምጃ ለተወሰደባቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረቦች ፤ ለደህንነትና የስቪል መሥሪያ ቤት ሃላፊዎች  ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እነርሱ መስዋዕትነት የከፈሉለትን ትግል ከዳር ለማድረስ ያለውን ቁርጠኝነት እያረጋገጠ ነው። ህወሃት በአማራ ክልል የጀመረው ትጥቅ የማስፈታት እርምጃም ሆነ የህዝባችንን ትግል ለመጨፍለቅ በሁሉም ክልሎች እየወሰደ ያለው አፈናና ግዲያ በምንም ተአምር ለነጻነታችን ከምናደርገው የትግል ጉዞ ለአፍታም ቢሆን እንደማያቆመንና የአገዛዙን ፍጻሜ እንደሚያቃርበው እርግጠኞች ነን።

የኢትዮጵይ ህዝብ የደርግን ሥርዓት ታገሎ ያሸነፈው፣ ደርግ “ፈጽም ወይም አትፈጽም” ብሎ የደነገገውን ህግ ተከትሎ እንዳልሆነ የያኔው የነጻነት ተጋዳላዮች የአሁኖቹ አምባገነን ገዦዎቻችን ዘንግተውታል። በዚህም ምክንያት በጥጋብና በእብሪት የመጨረሻ መውደቂያቸውን እንዳፋጠኑት ቀደምት አምባገነን መሪዎች ህወሃትም የመጨረሻው ጉዞውን እያፋጠነው ነው። ከኮማንድ ፖስቱ መጋረጃ ጀርባ ህዝባችን ላይ ግዲያ፣ እስር፣ አፈናና ስቃይ እየፈጠሙ ያሉ የህወሃት መሪዎች የድላችንን ቀን ያፋጥኑታል እንጂ አያዘገዩትም የምንለውም ለዚህ ነው።

ህገ ወጥ ትዕዛዝ ከአለቆቻችሁ ተቀብላችሁ ወገኖቻችሁ ላይ እስር፣ ግድያና ወከባ በመፈጸም ሥራ ላይ የተሰማራችሁ የአገራችን የመከላኪያ ሠራዊት፣ የፖሊስ፣ የደህንነትና የአጋዚ ጦር አባላት በሙሉ ! በህዝባዊ ተቃውሞ የአገዛዝ ዕድሜው ፍጻሜ እየተቃረበ የመጣውን አፋኝና ጨቋኝ አምባገነን ሥርዓት ዕድሜ ለማራዘም ብላችሁ በወገናችሁ ላይ  ከዛሬ ጀምሮ አንዳችም ጥይት እንዳትተኩሱ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያቀርብላችሁዋል። የናንተ የሥራ ዋስትና ለነጻነቱ ከህወሃት ጋር እየተፋለመ ያለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ በአገርና በህዝብ ሃብት ዘረፋ የከበሩ ጥቂት የህወሃት አመራሮች አንዳልሆኑ ከኦሮሚያ ፖሊስና ጸጥታ ሃይል አባላት ተማሩ! ከህዝብ አብራክ የወጣችሁ የህዝብ ልጆች መሆናችሁን የያዛችሁትን መሣሪያ በገዥዎቻችን ላይ በማዞር ዛሬውኑ በተግባር አስመስክሩ!

ለመብትህና ለነጻነትህ ከህወሃት አጋዚ ጦር ጋር እየተፋለምክ ያለሄው የአገራችን ወጣት!

እስር ፤ ግዲያና እንግልት መጠናከር ያስቆመው የነጻነት ትግል በአለም ታሪክ እንዳልነበረ ወደፊትም እንደማይኖር በጽናትህ እያስመሰከርክ ነውና እስከ መጨረሻዋ የድል ቀን ድረስ በጀመርከው ሁለገብ ትግል ግፋ! ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ሁሌም ከጎንህ ነውና !

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

አርበኞች ግንቦት 7